ሰኔ 13 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የቀድሞውን አዋጅ 780/2005ን ለማሻሻል የወጣው እና ሰኔ 10/2017 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው አዋጅ 1387/2017 መሰረት የሚደረገው የምርመራ ሂደት ከመደበኛው የወንጀል ምርመራ ሂደት በተለየ ዘዴ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ 780/2005ን ለማሻሻል የወጣው እና ሰኔ 10/2017 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው ረቂቅ አዋጅ 1387/2017 መሰረት አንድ መርማሪ በአስገዳጅ ሁኔታ ላይ ሲገኝ ከግድያ ወንጀል ውጭ ራሱን ለመከላከል ማንኛውንም አእርምጃ መውሰድ እንደሚችሉ መደንገጉ ይታወቃል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ከተለያዩ አካላት እየተነሱ ያሉ ስጋቶችን ተከትሎ የፋናንስ ደህንነትና አገልግለት እና ፍትህ ሚኒስቴር በጋራ በትላንትናው እለት ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የፋናንስ ደህንነትና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ እንዳሉት፣ በአዋጁ የተጠቀሰው ልዩ የምርመራ ሂደት ወይም በሽፋን የሚደረግ የወንጀል ምርመራ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት በመደበኛው የወንጀል ምርመራ ዘዴ ለማጣራት አዳጋች ሆኖ ሲገኝ እና ፍርድ ቤት እምኖ ትዕዛዝ ሲሰጥ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እነዚህም የምርመራ ሂደቶች የሚከናወኑት በወንጀል ድርጊት ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ እየደገፉ እንዳሉ ሲጠረጠር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዋጁ አመንጪ የሚባሉ 21 ወንጀሎችን በአባሪነት ያስቀመጠ፤ ብሎም ለትርጉም ተጋላጭ የነበሩ ጉዳዮችን በግልጽ የሚያስቀምጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡
በተሻሻለው አዋጅ 1387/2017 አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት በልዩ የወንጀል ምርመራ ሂደት መርማሪው ህይወቱን አደጋ ላይ ሲያገኝ፣ ነፍስ ከማጥፋት በስተቀር ራሱን የመከላከል ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ እንደሚችል መጽደቁ ይታወቃል፡፡
ስለዚህ አንቀጽ ማብራያ የሰጡት በፍትህ ሚኒስቴር የህግ ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አዲስጌትነት ተመስገን፣ በወንጀሉ ከተጠረጠረ ግለሰብ ወይም ቡድን ጋር ተመሳስሎ በመገኘት ወንጀሉን ለማጣራት የሚደረግ የምርመራ ዘዴ መሆኑን ጠቅሰው፣ የወንጀሉን ምንጭ ካገኘ በኋላ፣ ወንጀለኛውን ቁጥጥር ስር ለማድረግ በሚሞክርበት ጊዜ ህይወቱን አደጋ ላይ ሲያገኝ፣ ነፍስ ከማጥፋት በስተቀር ራሱን የመከላከል ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተር ጄነራሉ፤ መርማሪው የወንጀሉን ምንጭ ሳያገኝ ምንም አይነት እርምጃ መውሰድ እንደማይችል እና ቢወስድ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
አዋጁ እና እንዲህ ያለው የምርመራ ሂደት የሀገርን ሀብት ከብክነት ለመታደግ እንዲሁም ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚደረግ በፍርድ ቤት ሂደት እና ክትትል የሚከናውን መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጧል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ