ሰኔ 13 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን የመቆጣጠር እና የመከላከል አዋጅ 780/2005 እንዲሻሻል ያስገደደው ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ፋይናንስ ግብረ-ኃይል አባል በመሆኗ ነው ተባለ።
የዓለም አቀፉ ፋይናንስ ግብረ ኃይል በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የሚያስችሉ 40 ምክረ ሃሳቦችን የፈረመችው ኢትዮጵያ ከግብረ ኃይሉ ምክረ ሀሳቦች ጋር የሚጣጣሙ ህጎችን የማውጣት እና በየጊዜው የማሻሻል ግዴታ እንዳለባት የፋይናስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
እንደ ሀገር እነዚህን ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነቱ የኢትዮጰያ የፋናንስ ደህንነትና አገልግሎት ሲሆን፣ አገልግሎቱ ይህን ተግባራዊ ከሚያደርግበት ህጎች አንዱ የተሻሻለው አዋጅ 780/2005 መሆኑን የሚገልጹት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ናቸው፡፡
ላለፉት 12 ዓመታት አገልገሎት ሲሰጥ የቀየው ይህ የህግ ማዕቀፍ እንዲሻሻል ያደረገው ዋነኛው ምክንያት አትዮጵያ አባል የሆነችበት፣ የዓለም አቀፉ ፋይናንስ ግብረ ኃይል በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የሚያስችሉ 40 ምክረ ሃሳቦችን እያሻሻለ በመሄዱ እና አባል ሀገራትም በየጊዜው ከግብረ ኃይሉ ምክረ ሃሳቦች ጋር የሚጣጣም የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እና ማሻሻያ የማድረግ ግዴታ ስላለባቸው ነው ብለዋል፡፡
ህጉ ሲሻሻል እንዲያስፈጽሙት ኃላፊነት እና ስልጣን ከተሰጣቸው አካላት መረጃ በመሰበሰበብ ቀድሞ ለ12 ዓመታት አገልግሎት ላይ የነበረው አዋጅ ላይ የነበሩ የአፈጻጸም ክፍተቶች ምንድን ናቸው በሚለው ዙሪያ ዝርዝር ግምገማ ተደርጎ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በተደረገው ግምገማም የበፊቱ ህግ ላይ የግልጽነት ችግር እንደነበረበት መረዳት መቻሉን ገልጸው በቀድሞው አዋጅ ላይ በተለይ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽበርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል ላይ ከዋናው ወንጀል በፊት አመንጪ ወንጀል የሚባሉት በዝርዝር አለመቀመጣቸውን አንስተዋል፡፡
አክለውም በአዲሱ አዋጅ 1387/2017 ላይ አመንጪ ወንጀል ተብለው የተለዩ 21 ወንጀሎች በዝርዝር መካተታቸውንም አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ያብራሩት በትላንትናው ዕለት አገልግለቱ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በአዲሱ አዋጅ 1387/2017 ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት መድረክ ነው፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ