ሰኔ 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስር ካሉ ዞኖች መካከል አንዱ በሆነው ካማሺ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ 10 ዓመት እንዳለፈው ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት የክልሉ ምክር ቤት አባልና በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ኔኖ ናቸው።
ቦታው የህዳሴው ግድብ ውሃ 85 በመቶ የሚተኛበት፤ በርካታ አልሚዎች ያሉበት እንዲሁም ማዕድናት የሚመረቱበት ቢሆንም፤ አሁን ላይ በኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ኢንቨስተሮች የማልማት ፍላጎታቸው መቀነሱን ገልጸዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድቡ ሃይል ማመንጨት ጀምሮ ወደ ውጪ ሃገራት በመሸጥ ላይ ቢሆንም፤ የግድቡ ግንባታ እንዲጠናቀቅ ሲለፋ የነበረው ማህበረሰብ ለ10 ዓመት ኤሌክትሪክ እያገኘ አለመሆኑን አስረድተዋል።
ጥያቄው በክልል ምክር ቤት በተደጋጋሚ የቀረበ መሆኑንና እስካሁን የተሰጠ ተጨባጭ ምላሽ አለመኖሩን ገልጸዋል።
መናኸሪያ ሬዲዮ በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጠይቋል፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሪጅን ዳይሬክተር አቶ በከፎ ያለው በሰጡት ምላሽ፤ የተጠቀሰው ችግር ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎቱ መቋረጡን ገልጸው፤ ለመጠገን የተደረገው ሙከራም በጸጥታ ችግር ምክንያት መክሸፉን አስታውቀዋል፡፡
አሁን ላይ በዞኑ ያለውን ችግር በዘላቂ ለመፍታት ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ባሉ አከባቢዎች ያለውን ተመሳሳይ ችግር በተለያየ አማራጭ ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ በክልሉ ባልታወቁ ሃይሎች እየደረሰ ያለው ውድመት ተግዳሮት እየፈጠረ መሆኑን እና በቅርቡም መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ምላሽ ለማካተት በተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም፤ ክልሉን የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነ ገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ