ሰኔ 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በ2017/18 ዓ.ም የመኸር ወቅት የሚውል 21 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ቤት እየተጓጓዘ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በመጪው የመኸር ወቅት 20 ነጥብ 43 ሚሊየን ሔክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ659 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው።
በዚህም በበጋ መስኖ፣ በመኸር፣ በበልግና ሌሎች የሰብል ልማት አማራጮችን በማስፋት በግብርና ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመሬት ዝግጅት፣ የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ሥርጭት አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእርሻ ዝግጅት ከመደረጉ ቀደም ብሎ የማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙ አርሶ አደሩ በወቅቱ ግብዓት የሚያገኝበትን ዕድል እንደፈጠረ አንስተዋል።
በተያዘው የ2017/18 ዓ.ም በጀት ዓመት የመኸር ወቅትም የ21 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ኢትዮጵያ ተጓጉዞ በመሰረታዊ ማኅበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እንዲከፋፈል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የ2016/17 ዓ.ም በጀት ዓመት የሰብል ምርታማነትን ዕቅድ መነሻ በማድረግ የተሻለ የግብርና ልማት ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የአርሶ አደሮችን የግብርና ልማት ተነሳሽነት በማሳደግ በ20 ነጥብ 43 ሚሊየን ሔክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ650 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ መቀመጡን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው በመጪው የክረምት ወቅት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሥርጭት ይጠበቃል ብለዋል።
በመጪዎቹ የሐምሌና ነሐሴ ወራት በሚጠበቀው መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሥርጭት ለአርሶ አደሩ የግብርና ልማት ስራ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ተቋሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ጎርፍ ሊያጠቃቸው የሚችሉ ቦታዎችን በመለየት የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ አርሶ አደሩ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢዜአ
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ