ሰኔ 10 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የ”ትሮጃን ፈረስ” ተብሎ የተሰየመው የደም ካንሰር ሕክምና በእንግሊዝ የጤና አገልግሎት (NHS) በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ መቅረብ ጀመረ። ይህ ህክምና መርዛማ መድሃኒቶችን በካንሰር ህዋሶች ውስጥ በማስገባት የሚሰራ ሲሆን፣ ማይሎማ የተባለውን የደም ካንሰር ከአሁን ቀደም ከነበሩት ህክምናዎች በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ጊዜ ሊገታ ይችላል ነው የተባለው።
ይህ አዲስ መድሃኒት የላቀ የኬሞቴራፒ አይነት ሲሆን፣ በካንሰር ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው መድሃኒት በመጠቀም የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንደሚቀንስ ተገልጿል። ይህንን ህክምና ካገኙ የመጀመሪያ ሰዎች አንዱ የሆኑት የ60 ዓመቱ ፖል ሲልቬስተር፣ ህክምናው “ሕይወትን የሚቀይር” ነው ብለዋል፤ አሁን ደግሞ በታሪክ ጭብጥ የተነደፉ ጉዞዎችን እያቀዱ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
የደም ካንሰሩ እንዳለባቸው የተረጋገጠው ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን፣ ካንሰሩ በአከርካሪ አጥንታቸው ላይ ስብራት አስከትሎ ነበር። ባለፈው ዓመት የአጥንት መቅኒ ንቅለ ተከላ ቢያደርጉም በድጋሚ በሽታው ተመልሶባቸው እንደነበር ተመላክቷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ “ቤላንታማብ ማፎዶቲን” (belantamab mafodotin) የሚባለውን አዲስ ህክምና ቀደምት የመድሃኒት ተደራሽነት ፕሮግራም አካል በመሆን ሲወስዱ ቆይተዋል። በሳምንታት ውስጥ ደግሞ በሽታው እንደቀነሰላቸው ተረጋግጧል።
ፖል ህክምናው ከቤተሰባቸው ጋር ብዙ ጊዜ እንዲያሳልፉ አስችሏቸዋል ብለዋል። ሌሎች ህክምናዎች ለወራት በአልጋ ላይ እንዲገለሉ ያደርጓቸው እንደነበር የገለፁት ፖል፣ አዲሱ ህክምና ፍጹም ሕይወትን የሚቀይር እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህ ህክምና ኬሞቴራፒ መድኃኒት ከሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ጋር በሚመሳሰል ፀረ እንግዳ አካል (antibody) ጋር በመደመር ይሰራል። ፀረ እንግዳ አካላቱ በካንሰር ህዋሶች ላይ ያሉ ምልክቶችን እንዲለዩ ተደርገው የተሰሩ በመሆናቸው፣ ወደ ካንሰር ህዋሶች በመጓዝ ከገፃቸው ጋር እንደሚጣበቁና ከዚያም በውስጣቸው እንደሚዋጡ ነው የተነገረው፡፡
አንዴ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ የካንሰር ህዋሳትን ለመግደል የሚያስችላቸውን መርዛማ ንጥረ ነገር ይለቃሉ ሲል የዘገበው BBC ነው፡፡
በኢቫን ስለሺ
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ