ሰኔ 10 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የውጭ ሀገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለ ይዞታ የሚያደረጋቸው ረቂቅ አዋጅ ህገ መንግስታዊ መርሆችን ማዕከል በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ በትላንትናው እለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በተገኙበት የአስረጂ መድረክ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተካሄደ ሲሆን ፣ ከቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢና አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የፍትህ ሚኒስቴርና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮች አዋጁ ከህግ መንግስት መርሆች ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ወ/ሮ ሃና አርያስላሴ ከቋሚ ኮሚቴዎች በተለይም ከህገ መንግስቱ መርሆች ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ መሬት ለኢትዮጵያዊም ቢሆን የግለሰቦች ሳይሆን የጋራ መሆኑን በማብራራት የውጭ ዜጎች የቤት ባለይዞታነትን የሚከለክለው ህግ ህገ መንግስታዊ ሳይሆን በፍትሃብሄር ህግ ላይ የተደነገገ መሆኑን በማመላከት ይህንን ማሻሻል እንደሚቻል አስረድተዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው አዋጁ የተዘጋጀው በዘርፉ ተጨማሪ ሃብት ለመፍጠር እንደሆነና በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ በማመላከት የሌሎች ሀገራት ልምድ በሚገባ መታየቱንና በጎረቤት ሀገራት አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሀምሳ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ዶላር በማቅረብ ቤት ለመግዛት ካመለከተ እንደሚፈቀድ ጠቁመዋል። አክለዉም ዜግነትን ለሌላ ሃገራት ዜጎች የሚሰጡ ሀገራት መኖራቸውን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከባህልና እሴት እንዲሁም ከመጣንበት መንገድ አንፃር ስጋቶች መቅረባቸው አግባብ ቢሆንም ፣አዋጁ መውጣቱ የሀገሪቷ ዜጎች ላይ በልዩነት የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደሌለና ቢኖር እንኳ ታይቶ በመመሪያና ደንብ ማስተካክያዎችን መወሰድ እንደሚቻል አፅኖት ሰጥተዋል።
የቤት ፍላጎት በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ሆኖ ሳይዳረስና ምላሽ ሳይሰጠው የውጭ ሀገራት ዜጎች መግባታቸው አግባብ ነው ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ወ/ሮ ጫልቱ እኛን ያገደን የአቅም ጉዳይ እንጂ የትኛውም ሰው የቤት ባለቤት መሆን ይችላል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የውጭ ዜጎች ምን ያህል የቤት ባለቤት መሆን እንደሚችሉ በቁጥር በቀጣይ ጊዜ ታይቶ እንደሚቀመጥ ገልፀዋል።
በቀጣይም ከምክር ቤተ የተሰጡ አስተያየቶች ታክሎበት ለዉይይት ረቂቁ እንደሚቀርብ ተመላክቷል ።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ