ሰኔ 10 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ የበርካታ ጋዜጠኞቹ የኢሜይል አካውንቶች ላይ የደረሰን የሳይበር ጥቃት እያጣራ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል። ጥቃቱ ሐሙስ ዕለት የተገኘ ሲሆን፣ ጋዜጣው ወዲያውኑ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
እንደ ጥንቃቄ እርምጃ፣ የጋዜጣው ሁሉም ሰራተኞች የይለፍ ቃላቸው ዓርብ ዕለት ዳግም እንዲታደስ ተደርጓል። ጥቃቱ በሌሎች የፖስት ሲስተሞች ወይም በደንበኞች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ ባይታወቅም ፣ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው ከሆነ ጥቃቱ የውጭ መንግስት ስራ ሊሆን ይችላል።
ጥቃቱ የጋዜጠኞችን ማይክሮሶፍት አካውንቶች በማጥቃት ለጥቃት አድራጊዎቹ የስራ ኢሜይሎችን የማግኘት እድል እንደሰጠ ተገልጿል። ኢላማ ከተደረጉት ጋዜጠኞች መካከል የብሔራዊ ደህንነትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቡድን አባላት እንዲሁም ስለ ቻይና የሚጽፉ ዘጋቢዎች ይገኙበታል።
እ.ኤ.አ. በ2022 የዎል ስትሪት ጆርናል አሳታሚ የሆነው ኒውስ ኮርፕ ተመሳሳይ የዲጂታል ሰርጎ ገቦች ጥቃት ደርሶበት የበርካታ ጋዜጠኞች ኢሜይል አካውንቶች ተጥሰው እንደነበር ይታወሳል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው ።
በኢቫን ስለሺ
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ