እስራኤል እና ኢራን ለሶስተኛ ተከታታይ ቀን ጥቃቶችን እየተለዋወጡ ሲሆን፣ ሁለቱም ሀገራት ለአጥቂነት ምላሽ መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ይህ ውጥረት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እየተባባሰ መምጣቱን ያሳያል።
🔰በእስራኤል ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች እና ጉዳቶች
እሁድ ምሽት በቴል አቪቭ እና በኢየሩሳሌም ሰማይ ላይ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል፤ የእስራኤል የብረት ጉልላት (Iron Dome) ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን መትቶ መውደሙን አስታውቋል።
ቅዳሜ ምሽት ላይ በተፈፀሙት ጥቃቶች አስር ሰዎች የተገደሉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ህፃናት መገደላቸውን እና ከ100 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በባት ያም ከተማ የሚገኝ አንድ ባለ 10 ፎቅ አፓርታማ ማለዳ ላይ ተመቶ ስድስት ሰዎችን ለህልፈት መዳረጉ የተገለጸ ሲሆን ከሟቾች መካከልም የአስር ዓመት ወንድ ልጅና የስምንት ዓመት ሴት ልጅ ይገኙበታል ነው የተባለው።
እንዲሁም በሰሜናዊቷ የአረብ ከተማ ታምራ ላይ በደረሰው የኢራን ጥቃት አራት ሰዎች መሞታቸውን የድንገተኛ አገልግሎት ሰራተኞች እና የአካባቢው ሆስፒታል ገልጸዋል።
🔰በኢራን ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች እና ጉዳቶች
እስራኤል የቴህራን ከተማን ጨምሮ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ኢላማዎችን መምታቷን ገልጻለች። የኢራን መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ፣ ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ 128 ኢራናውያን ሲገደሉ 900 ያህል ሰዎች ቆስለዋል።
እስራኤል መጀመሪያ ላይ የኢራንን የኒውክሌር መሰረተ ልማት እና ሌሎች ኢላማዎችን አርብ ዕለት ማጥቃቷን አስታውቃ ነበር።
የቢቢሲ ጋዜጠኞች በኢራን መንግስት በተጣለባቸው ገደቦች ምክንያት ከኢራን ውስጥ ዘገባ ማቅረብ ባለመቻላቸው፣ በእስራኤል ጥቃት የደረሰውን ጉዳት በትክክል ለመገምገም አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ቢቢሲ ዘግቧል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ (Benjamin Netanyahu) የጥቃቱ ቦታን ከጎበኙ በኋላ፣ ኢራን “ሆን ብላ በፈፀመችው የሲቪሎች፣ የሴቶችና የህፃናት ግድያ” “ከፍተኛ ዋጋ” እንደምትከፍል አስጠንቅቀዋል።
በሌላ በኩል፣ የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ቴል አቪቭ፣ ሃይፋ እና ሌሎች ከተሞችን “በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ የኢራን ሚሳኤሎች እና ድሮኖች” ማጥቃቷን አስታውቋል።
የኢራን የነዳጅ ሚኒስቴር ደግሞ በቴህራን የሚገኘው የሻህራን የነዳጅ ማከማቻ እስራኤል በሰነዘረችው ጥቃት መመታቱን ገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (IDF) የቴህራን የጦር ሰራዊት ሚኒስቴርን እና “የኢራን አገዛዝ የኒውክሌር መዝገብን የደበቀባቸውን ተጨማሪ ኢላማዎች” ጨምሮ ከ80 በላይ ኢላማዎችን በሌሊት መትቶ እንደነበር አስታውቋል።
በሰሜን ምስራቅ ማሽሃድ ከተማ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ላይ ነዳጅ የሚሞላ አውሮፕላንም ተመቷል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ለኢራን ህዝብ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በፋርስኛ ጽፎ፣ ለራሳቸው ደህንነት ሲባል ከሁሉም የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋሲሊቲዎች እንዲርቁ እና ተጨማሪ ማስታወቂያ እስከሚሰጥ ድረስ እንዳይመለሱ አስጠንቅቋል።
ምላሽ ይስጡ