በቀሪ የሀገራዊ ምክክር ሂደት የምሁራን ሚና ከፍ ማለት እንዳለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ ባካሄደው ውይይት አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ዛሬ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ባዘጋጀው ከምሁራን ጋር የተደረገ ውይይት ምሁራን በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ሃሳባቸውን በማዋጣት ሚናቸውን ማላቅ እንዳለባቸው አስታውቋል።
እስከዛሬ ሲካሄዱ ለቆዩትና ቀሪ ለሚከናወኑት ሀገራዊ ምክክሮች በሚዛናዊ እውቀት የዳበረ ምክረ ሃሳብ ከምሁራን ይጠበቃል ሲሉ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ተናግረዋል። ምሁራን ከልምድና ከጥናት እና ምርምሮቻቸው በመነሳት ለግጭቶች መፍትሄ ማምጣት እንደሚገባቸው ኮሚሽነሩ አክለው ገልጸዋል።
ሰላም አጥ በሆኑ አካባቢዎች ታጣቂዎችንም ያካተተ ምክክር እንዲካሄድ የተሻለ እውቀት ባለቤት የሆኑት ምሁራን ሃሳብ እንዲያዋጡ የተደረገ ውይይት ነው ሲሉ ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል። አክለውም ትርክትና ታሪክ ወለድ ችግሮች አሉ ያሉት ኮሚሽነሩ እነዚህን መሰል ችግሮች እንደ ሀገር እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ምሁራን ሃሳብ ማዋጣት አለባቸው ሲሉም አብራርተዋል።
በቀጣይ ከዲያስፖራውና በትግራይ ክልል በሚደረገው የምክክር ሂደትም የምሁራን ተሳትፎ ለኮሚሽኑ ሁነኛ አዎንታዊ ግብዓት እንደሚሆንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቀጣይ ከዲያስፖራውና በትግራይ ክልል ምክክሩን የሚያደርግ ሲሆን ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ ስለመሆኑም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ምላሽ ይስጡ