በተለያዩ ጊዜያት በሀገሪቱ የተከሰቱትን ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተከትሎ በርካታ ዜጎች በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ቀጣዩን የክረምት ወቅት ተከትሎ አስፈላጊው ጥገና የማይደረግላቸው ከሆነ ከፍተኛ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አሊ ሰይድ፤ በክልሉ 11 የሚጠጉ መጠለያ ጣቢያዎች ቢኖሩም፤ ከ2ቱ በስተቀር ሌሎቹ በክረምቱ የሚኖረውን ጫና መቋቋም የማይችሉ ናቸው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ከወዲሁ የጥገና ስራ ሊሰራላቸው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በክልሉ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋን ተከትሎ ከ34ሺ በላይ ተፈናቃዮች በዞኑ እንዳሉ የገለጹት ኃላፊው፤ 14ሺ የሚሆኑት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለዓመታት መኖራቸውን ገልጸው፤ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ብለዋል፡፡ ዞኑ በአቅሙ ልክ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ጣቢያዎች እየለየ መሆኑን ያስታወቁት ኃላፊው፤ ተላላፊ በሽታዎች ስጋት በመሆናቸው ከጤና ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአዲግራት፤ ሽረ፤ መቀሌ እና በሌሎች አካባቢዎች የመጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉ የገለጹት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር አቶ ጣዕመ አረዶም፤ ካንፖቹ ለወረርሽች ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጠለያ ጣቢያዎቹ የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም፤ በቂ ነው የሚባል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣዩ የክረምት ወቅት የከፋ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመጠለያ ጣቢያዎቹ ከወዲሁ እንዲጠገኑ ጥያቄዎች ቢቀርቡም፤ አጥጋቢ ምላሽ እየተሰጣቸው እንዳልሆነ ክልሎቹ አስታውቀዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ