በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት በኤም ፖክስ በሽታ የተጠቁ ሰዎችን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸው የኦሮሚያ ክልል አስታውቋል፡፡ በኤም ፖክስ 8 ሰዎች መያዛቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ድንገተኛ ጤና ቁጥጥርና የጤና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ሹሚ በኤም ፖክስ የተጠቃ የመጀመሪያ ሰው በክልሉ መገኘቱን በማስታወስ አሁን ላይ ስርጭቱ እንዳይስፋፋ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማትን በሰው ሀይልና በሌሎችም መንገዶች ዝግጁ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን በማንሳት አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የምርመራ ስራ መጀመሩን አመላክተዋል፡፡
ከታማሚዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ቤት ለቤት በመሄድ ማስተማርና ምርምራ እንዲያደረጉ መደረጉን የገለፁት ዳይሬክተሩ ሰዎች ግንዛቤው ኖሯቸው ከበሽታው እራሳቸውን እንዲከላከሉ በመገናኛ ብዙሀንና ሌሎችም አማራጮችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ምላሽ ሰጪ ግብረ ሀይል በማዋቀር ስርጭቱን እንዳይስፋፋ እየተደረገ መሆኑን የገለፁ ሲሆን በተለይ በክልሉ የበሽታው መመርመሪያ ላብራቶሪ እጥረት እንዳይኖር የሚሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡
ኤም ፖክስ በኦሮሚያ ክልል ስጋት ቢሆንም የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ አስቀድሞ በትምህርት ቤቶች፤በትራንስፖርት እና በሌሎችም ስፍራዎች ጥንቃቄ እንዲደረግ ስራዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በኬኒያ የበሽታው ስርጭት መኖሩን ተከትሎ በኮንትሮባንድ መንገድ የሚገቡ አልባሳትና ሌሎች እቃዎች ስርጭቱ እንዲስፋፋ መንስኤ እንዳይሆኑ ቁጥጥር ከማድረግ ባሻገር ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የማስተማር ስራ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ለኤምፖክስ በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች ተብለው ከተለዩት መንገዶች መካከል በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር የሚደረግ የሰውነት ንክኪ፣ የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲሁም ከታማሚ ሰው ጋር ንክኪ ያለውን ቁስ በጋራ መጠቀም በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ