ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሚያደርጋት የቁም እንስሳት ሃብት ቢኖራትም በገቢ ደረጃ ግን በሚፈለገው ልክ እንዳልተጠቀምንበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
የተቀቀለ ስጋን ወደ ውጭ ሃገራት መላክ ከተጀመረ 3 አመታትን እንዳስቆጠረና ሃገሪቱም ገቢ እያገኘችበት እንደሆነ የገለጹት በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ አዲስ እጅጉ ናቸው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በስጋ ምርት ተወዳዳሪ ለመሆን ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዘርፉን ለማነቃቃትና ለሃገርም የተሻለ ገቢ ለማስገኘት በተለያዩ አካባቢዎች አማራጭ የስራ ቦታዎችን በማስፋፋት ባለሙያዎችንም በማሰልጠን እየሰራ ቢሆንም አሁንም ድረስ የብቁ ባለሙያ እጥረት እንዳለበት ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡
የስጋ ምርት በባህሪው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ መሆኑን የገለጹት የኮምኒኬሽን ስራ አስፈጻሚው፣ አሁን ላይ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥራትና ደህንነት ላይ በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ከኢትዮጵያ በስፋት የተቀቀለ ስጋን እንደሚረከቡ ያስታወቁት የኮምኒኬሽን ስራ አስፈጻሚው፣ በአንድ አመት ውስጥ ከበሬ፣ ከፍየልና በግ 15ሺህ ቶን ስጋ ለመላክ ታስቦ እስካሁን ከ15ሺህ 300 በላይ የተቀቀለ ስጋ መላክ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ዘርፉ ከፍተኛ ጥራት እና ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ ባለስልጣኑ ችግሩን ለመፍታት ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ