ሽብርተኝነትን እንዋጋ ስትል ህንድ ለኢትዮጵያ ጥሪ ለማቅረብ ከገዢው እና ተቃዋሚ ፓርቲ የተውጣጡ የምክር ቤት አባላት ልዑክን ወደ ኢትዮጵያ መላኳን በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ አስታውቋል።
በፓኪስታን መንግስት የሚደገፉ ታጣቂ ሃይሎች በሺዎች በሚቆጠሩ ንጹሃን ህንዳውያን ላይ የሽብር ተግባር ፈጽመዋል በማለት ከሁሉም ፓርቲዎች የተውጣጡ የህንድ የፓርላማ አባላት ትላንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ባለው የህንድ ኤምባሲ ተገኝተው አስታውቀዋል።
ልዑካኑ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ግንባር ቀደም ሀገር በመሆኗ ከህንድ ጎን እንድትቆም ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።
እንደ አህጉርም የአፍሪካ ህብረት ከየትኛውም አህጉራዊ ድርጅት በበለጠ በሽብርተኝነት ላይ ቁርጠኛ አቋምና መመሪያ ያለው ነው ያለው ልኡካን ቡድኑ፤ አፍሪካም ከህንድ ጎን እንድትቆም ጥሪ አስተላልፏል።
ልዑኩ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግሮ ኢትዮጵያ ከህንድ ጎን እንደምትቆም ስለመጠየቁ ያስታወቀ ሲሆን zero tolerance against terrorism በሚል መሪ ቃል ባከናወነው የትላንቱ ጉባኤው፤ ለመላው አፍሪካውያንና የአፍሪካ ቀንድ ጥሪውን አስተላልፏል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ፤ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ከአፍሪካ ጋር መስራት ነው ያለው ኤምባሲው፤ ህንድ የኢትዮጵያን አስቸኳይ አጋርነት እንደምትሻ አስታውቋል።
ከህንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጣው ልኡካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በቱርክና በደቡብ አፍሪካ ለተመሳሳይ አላማ አቅንቶ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይ በግብጽ እና በሌሎች የተመረጡ 5 የአፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ ጥሪዎችን እንደሚያከናውኑ አስታውቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ