በየአመቱ ከሚከናወኑ እና የክለቦች ፉክክር ከሚደምቅበት እንዲሁም በአውሮፓ ውስጥ ሀያሉ ክለብ ለመባል የሚደረግ የክለቦች ትንቅንቅ በተለያዩ የአውሮፓ ግዙፍ ስቴዲየሞች በባውዛ ደምቆ ሲከናወን የቆየው የክለቦች ትልቁ የውድድር መድረክ የሆነው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በፓሪስ ሴንት ጄርሜ እና በኢንተርሚላን መካከል የሚከናወን ይሆናል።
70ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ነው በዛሬው እለት የሚከናወነው። ስያሜውን ወደ አውሮፓ ሻምፓዮንስ ሊግ ከቀየረ በኋላ ደግሞ የዘንድሮው ውድድር ለ33ኛ ጊዜ ያደርገዋል። የዘንድሮ ለየት ባለ መልኩ ተሳታፊ ቡድኖችን ወደ 36 ከፍ አድርጎ የሊግ ባህሪ እና የጨዋታ ቅርፆን ይዞ 1 ቡድን በሜዳው 4 ጊዜ ከሜዳው ውጪ 4 ጊዜ ጨዋታውን አድርጎ በሚያገኘው ነጥብ መሰረት ቀድመው የሚያልፉ 8 ቡድኖች ከቀሪዎቹ በጥሎ ማለፍ ቋት ውስጥ ከገቡ እና ከ9ኛ እስከ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ቡድኖች በደርሶ መልስ ጨዋታቸውን አድርገው ከሚለዩ 8 ቡድኖች ጋር በጥሎ ማለፉ እንዲገናኙ በሚል ባመጣው አዲስ የአጨዋወት መንገድ መሰረት የተከናወነ የውድድር ምዕራፍ ሲሆን በእግርኳስ ወዳዱ ቤተሰብ ተቀባይነት አጊንቷል ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ባይቻልም ግን ተወዳጅነት እና ተጠባቂነቱ ሳይቀዘቅዝ ለግዙፉ ዋንጫ ሁለቱን ክለቦች አፋጥጧል።
ፓሪስ ይሄንን ዋንጫ አሳክተውት አያውቁም ፤ ኢንተርሚላን በበኩላቸው በታሪካቸው ለ4ኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማሳካት ነው በሙኒክ የሚፋጠጡት ኢንተርሚላን ለመጪረሻ ጊዜ ዋንጫውን ያሳኩት በ2ዐ10 ሲሆን ከ15 አመት በኋላ ዳግም ዋንጫውን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።
ሁለቱም ቡድኖች ለፍፃሜው ደርሰው ዋንጫውን በማጣት ቅስማቸው ተሰብሮ አይተውታል የፈረንሳዩ ሀያል ቡድን PSG በ2020 በባየርሙኒክ ሲሸነፉ ኢንተርሚላን በበኩላቸው በ2023 በማንቸስተር ሲቲ በመሸነፍ ዋንጫውን ጨብጠው የለቀቁ ፤ አይተው የተነፈጉ ቡድኖች የሚያደርጉት ትንቅንቅ ከወዲሁ የእግርኳስ ቤተሰቡን ቀልብ ስቧል።
ከዚህ ጨዋታ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ቁልፍ የሆኑ ቁጥራዊ መረጃዎችን ለመመልከት ያህል :-
አሰልጣኝ ልዊስ ኤንሪኬ በ2014/15 ከባርሴሎና ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ማሳካት የቻለ ሲሆን በዚ አመትም ከፓሪስ ጋር ይህንን ዋንጫ በማሳካት በታሪክ ሁለት የተለያዩ ክለቦችን በመያዝ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ክብርን ማሳካት የቻለ 7ኛ አሰልጣኝ ለመሆን ጥረት ያደርጋል።
የባየር ሙኒክ ስቴዲየም የሆነው አሊያንዝ አሬና ከ2012 በኋላ የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታን ሲያሰናዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደርገዋል።
የፈረንሳዩ ሀያል ቡድን ፓሪስ ሴንት ጄርሜ ከጣልያን ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው ያለፉት 11 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያጋጠማቸው 1 ጊዜ ብቻ ነው። እሱም በ2023 ህዳር ወር በኤሲሚላን 2-1 የተሸነፉበት አጋጣሚ ይታወሳል።
በዚህ መርሀ ግብር ሀገራቸውን ወክለው ይሄንን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያሳኩ ተጫዋቾች በሁለቱም ቡድኖች መካከል ይኖራሉ ከኢንተርሚላን 5 ተጫዋቾች ማለትም አስላኒ ከአልቤኒያ ፤ ሚኪቴሪያን ከአርሜኒያ ፤ ሜህዲ ታሬሚ ከህንድ ፤ ሀካን ቻላኖግሉ ከቱርክ ሲሆኑ ከፓሪስ ሴንት ጄርሜ በኩል ደግሞ 3 ተጫዋቾች ማለትም ዊሊያን ፓቾ ከ ኤኳዶር ፤ ሊ ካንግ ኢን ከደቡብ ኮሪያ እንዲሁም አችራፍ ሀኪሚ ከሞሮኮ ይሄንን አድል ሊያገኙ ይችላሉ።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍፃሜ በቅተው ዋንጫውን 13 ጊዜ ያሳኩ ጣልያናዊ አሰልጣኞች አሉ በውድድር መዶረኩ ከፍተኛ ቁጥር ነው የኢንርሚላኑ አሰልጣኝ ፤ ሲሞኒ ኢንዛጊ ቁጥሩን ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
የጣልያን እና የፈረንሳይ ተወካይ ቡድኖች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ሲገናኙ ከ1993 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደርገዋል። ያኔ ኦሎምፒክ ዴ ማርሴ ኤሲ ሚላንን በመርታት ዋንጫውን ማሳካታቸው ይነገራል።
ፓሪስ ሴንት ጄርሜ በታሪካቸው ይህንን ዋንጫ ከፍ አድርገው አሳክተውት አያውቁም ፤ ዛሬ ድል ከቀናቸው ይህንን ዋንጫ ማሳካት የቻለ አዲስ 24ኛ ክለብ ሆኖ ይመዘገባል።
የፈረንሳዩ ሀያል ቡድን PSg በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታቸውን 0-0 ካጠናቀቁ 98 ጨዋታዎች አልፈዋል። ለመጨረሻ ጊዜ ምንም ጎል ያላስቆጠሩት በ2015/16 የውድድር ዘመን ከሪያል ማድሪድ ጋር ባደረጉት የምድብ ጨዋታ እንደነበር የሚታወስ ነው። ስለዚህ በዛሬውም ጨዋታ ጎል ሊያስቆጥሩ እንደሚችሉ ይገመታል።
ኢንተርሚላን ባርሴሎናን አስገራሚ በሆነ መልኩ በድምር ውጤት 7-6 አሸንፈው በዚህ የውድድር መድረክ ላይ በርካታ ጎሎች የተቆጠሩበት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ሆኖ ለፍፃሜው መብቃታቸውን ሲያረጋግጡ ፓሪስ ሴንት ጄርሜ በበኩሉ አርሰናልን በድምር ውጤት 3-1 በመርታት ነው ለፍፃሜው የበቁት።
የዛሬውን የፍፃሜ ጨዋታ የሚያሰናዳው የባየር ሙኒኩ ስቴዲየም አሊያንዝ አሬና ላይ ፓሪስ ሴንት ጄርሜ ጥሩ ሪከርድ የለውም ፤ በታሪኣቸው ባደረጓቸው 17 ጨዋታዎች 9ኙን ሲሸነፉ 5ት ጊዜ ብቻ ነው ድል የቀናቸው። በዚህ አመት እንኳስ በምድብ 5ኛ ጨዋታ በባየርሙኒክ 1-0 የተሸነፉት እዚሁ አሊያንዝ አሬና ስቴዲየም ላይ ነው።
ኢንተርሚላን በዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ጉዞአቸው 14 ጨዋታ አድርገው 1 ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፉት ፤ 10 ሩን አሸንፈዋል አጥቂአቸው ላውቴሮ ማርቲኔዝ 9 ጎል ያስቆጠረ ሲሆን ዛሬ በፍፃሜው ተጨማሪ 1 ጎል ማስቆጠር የሚችል ከሆነ ሄርናን ክሪስፖ በ2002/03 ተይዞ የነበረውን ሪከርድ የግሉ ማድረግ ይችላል።
ጨዋታውን ከ2010 ጀምሮ በዳኝነት ተመዝግብ በስራ ላይ የሚገኘው ኮቫክስ የሚመራው ይሆናል ፤ ሮሜንያዊ ዜግነት ያለው ይህ ዳኛ የፍፃሜ ጨዋታ ሲዳኝ ለ3ኛ ጊዜ ያደርገዋል ፤ ከዚህ በፊት አምና በዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ አየርላንድ ደብሊን ከተማ ላይ በአታላንታ እና በሌቨርኩስን መካከል የተደረገውን የአታላንታ እና የሌቨርኩዝን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት መምራቱ እንዲሁም በ2022 የኮንፈረንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ አልቤኒያ ቲራና ከተማ ላይ በሮማ እና ፌይኖርድ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት መምራቱ አይዘነጋም።
በዚህ አመት በሊቨርፑል እና ፓሪስ ሴንት ጄርሜ መካከል የደረገውን የጥሎ ማለፍ ጨዋታን ጨምሮ በቱርክ የኢስታንቡል ደርቢ በጋላታሳራይ እና ፌነርባቼ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በገለልተኛ ዳኛ እንዲካሄድ ታስቦ በእንግድነት ተመራጭ ሆኖ ተጋብዞ መዳኘቱ አይዘነጋም።
ባለፉት 3 አመታት ለሁለተኛ ጊዜ ለፍፃሜ የበቃው ኢንተርሚሊን ከ2019/20 የውድድር ዘመይ ለፍፃሜ ከበቃው ፓሪስ ሴንት ጄርሜ ጋር የሚያደርጉት አለም በጉጉት የሚጠብቀው የሁለቱ ክለቦች ፍጥጫ ዛሬ ምሽት 4:00 አሊያንዝ አሬና ላይ ማላሽ መስጠት ይጀምራል።
ታዋቂው ባንድ ሊንከን ፓርክ እንደ አዲስ ያቀናበሩትን ነምብ የተሰኘ ሙዚቃቸውን በፍፃሜው እንደሚያቀርቡት ተገልጿል::
በሚካኤል ደጀኔ
ምላሽ ይስጡ