ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ጠብ አጫሪ ንግግር ከሰላማዊ አማራጭ ያለፈ ምላሽ እንደማትሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
እንደ ሀገር የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መርህ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ መኖር በሚያስችል አግባብ የተቀረጸ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ተናግረዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ እየተነገሩ ለሚገኙ ጠብ አጫሪ ንግግሮች ኢትዮጵያ ምላሽ በመስጠት አትጠመድም ያሉት ቃል አቀባዩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ትብብርን በደገፈ ሁኔታ የሚቀጥል ስለመሆኑ ገልጸዋል።
አሁንም በቀጠናው ሰላማዊ አማራጭን በመከተል ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቁ ሂደት ይቀጥላል ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የባህር በሩ ጥያቄም የህልውና ጉዳይ መሆኑ እንደ ሀገር የተያዘ አቋም በመሆኑ ጉዳዩን እውን ለማድረግ ሰላማዊ ቀጠናዊ አማራጮች የሚተገበሩ ይሆናል ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በትንኮሳና በጠብ አጫሪ አካሄድ ለማሰናከል የሚሞክሩ ጎረቤት ሀገራት ቢኖሩም ሰላማዊ አማራጭ ቋሚ የኢትዮጵያ መርህ ነው ሲሉ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ተናግረዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ