ሶስት የቀድሞ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ተሽከርካሪዎችን በመስረቅ ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ሁለት ተሽከርካሪዎችን በመስረቅ ክስ የቀረበባቸው ሶስት የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ዘጠኝ ተከሳሾችን ጥፋተኛ ሲል ወስኗል።
ተከሳሾቹ 1ኛ በአዲስ አበባ ፖሊስ የአራዳ ክፍለ ከተማ አራት ኪሎ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መከላከል ቡድን መሪ የነበረው ዋና ሳጅን ትግሉ ሰቦቃ፣ 2ኛ እና 3ኛ ደግሞ በአዲስ አበባ ፖሊስ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የጊቢ ጥበቃ አባላት የነበሩት ኮ/ብል ዘነበ ኩማ እና ኮ/ብል መንግስቱ እንቻሌ እንዲሁም 4ኛ አቶ ላዕከ ተስፋ፣ 5ኛ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት የቦሌ አራብሳ ፕሮጀክት 13 ጥበቃ የነበረው መልካሙ አያና፣ 6ኛ መላኩ ካላዩ፣ 7ኛ ከበደ ገ/ኢየሱስ፣ 8ኛ ወንዶሰን ወይም ኢብራሂም ረጋሳ እና 9ኛ ሮቤል ሙሉዓለም ናቸው።
ተከሳሾች የማይገባቸውን ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ቦሌ አራብሳ ፕሮጀክት 13 ውስጥ በጥበቃነት ከሚሰራው 5ኛ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር የወንጀል ድርጊት መፈፃማቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።
ተከሳሾቹ በዋና እና ልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው ቦሌ አራብሳ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የድርጅቱ የጥበቃ ሰራተኛ ሥራ ላይ ተሰማርቶ በድርጅቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከ4ኛ ተከሳሽ ጋር በመነጋገር ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተከሳሽ የፖሊስ አባላት በዕለቱ የጥበቃ ተረኛ ሰራተኛ የሆነውን ግለሰብ ለጥያቄ ትፈለጋለህ በሚል ከጥበቃ ሥራው ይዘውት መሄዳቸው በክሱ ሰፍሯል።
የዐቃቤ ሕግ ምስክርና በዕለቱ በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው ግለሰብ ቦታውን የሚጠብቅልኝ ሰው ደውዬ ልጥራ ሲል 2ኛ እና 5ኛ ተከሳሽ በቦታው ቀርተው እኛ እንጠብቃለን አንተ ሂድ ማለታቸው በክሱ ዝርዝር ቀርቧል።
በዚህም 4ኛ ተከሳሽ የዋጋ ግምቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ ሲኖትራክ ሞተሩን ያለ ቁልፍ በማስነሳት ከቦታው ይዞ ወጥቷል። እንዲሁም 6ኛ ተከሳሽ በተመሳሳይ የዋጋ ግምቱ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ ሲኖትራክ ከቦታው ይዞ መውጣቱ ተጠቅሷል።
7ኛ ተከሳሽ ደግሞ መንገድ ላይ ጠብቆ በመቀላቀል መኪናዎቹን በሌላ ተሽከርካሪ አጅበው ወደ ኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በማቅናት ተሽከርካሪዎቹን ለ8ኛ ተከሳሽ ማስረከባቸው በክሱ ተገልጿል።
በዚህም 8ኛ ተከሳሽ ለቀሪ ተከሳሾች የአልጋ አበል በመክፈል ለአንደኛው ተሽከርካሪ ሽያጭ በሚል 600 ሺህ ብር በአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ በኩል ወደ 7ኛ ተከሳሽ የባንክ አካውንት ገቢ ማድረጉ በክሱ ዝርዝር ላይ ቀርቧል።
በጠቅላላ የዋጋ ግምታቸው 11 ሚሊየን ብር የሆኑትን ሁለት ተሽከርካሪዎች መብት ሳይኖራቸው በህገወጥ መልኩ ወስደው በመሰወር የተሽከርካሪዎቹ ህጋዊ ባለቤት ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሱ በመሆኑ በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ተከሶሾቹ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።
ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ሲሆን÷ በዚህም ችሎቱ በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ላይ 6 ዓመት ፅኑ እስራት እና 7 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ቅጣት አስተላልፏል።
5ኛ፣ 8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች በሌሉበት 10 ዓመት እና 50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑን የፌደራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ