እ.ኤ.አ ሜይ 25/2025 ሪፖርተር ጋዜጣ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያለበት የውጭ ዕዳ መጠን ከ575 ዶላር መድረሱ ተነገረ” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ያወጣው ሪፖርት ገለጸ በማለት ዘገባ መታተሙ ይታወሳል።
ዘገባው ላይ ግድፈቶች ያሉት በመሆኑ እንዲሁም ትክክለኛውን አውድን ማሳወቅ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል።
ዘገባው ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ማህበሩ ያወጣውን ሪፖርት በማጣቀስ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ እስከ 2023 ድረስ ያለባት የብድር መጠን 62.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና “እያንዳንዱ ኢትጵያዊ የተጠቀሰው መጠን የውጭ ብድር ዕዳ” እንዳለበት ይገልጻል።በዘገባው ኢትዮጵያ ያለባት የውጭና የሀገር ውስጥ የብድር መጠን ተለይቶ መቅረብ ሲገባው በተጠቀሰው ጊዜ የነበረው የውጭ ዕዳ መጠን 28.5 ቢሊዮን ዶላርን 62.5 ቢሊዮን ዶላር ብሎ ማቅረብ የተሳሳተ ነው።
እ.ኤ.አ እስከ 2024 መጨረሻ ድረስ ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ የብድር መጠን የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ጨምሮ 31.6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡
በተጨማሪም የሀገሪቱን የውጭ ብድር በተመለከተ አውዳዊ ማብራሪያ (contextual background) ለመስጠት ያህል፣ የኢትዮጵያ የውጭ ብድር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የተጠራቀመ ውርስ ዕዳ (legacy debt) ሲሆን የዕዳ ጫና በዚህ ምክንያት የተባባሰ መሆኑ ይታወቃል። ላለፉት ሰባት ዓመታት ይህንን ውዝፍ ዕዳ ያስከተለውን የክፍያ ጫና ለመቀነስ በመንግስት በኩል የተደረጉ ወሳኝ ጥረቶችን መጥቀስ አስፈላጊ ነው።
1.መንግሥት ባለፉት በርካታ ዓመታት ምንም የውጭ የንግድ ብድር ያልወሰደ ሲሆን ለልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የውጭ ብድር ሲወስድ የነበረው በአብዛኛው ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና ከመንግሥታት ከሚገኙ ብድሮች በመሆኑ የብድር ጫናን የማያስከትሉና ወለድ የማይታሰብባቸው በሌላ አገላለጽ በጣም ዝቅተኛ ወለድ እና ረዥም የእፎይታና የክፍያ ጊዜ ያላቸው ብድሮች (concessional loans) ናቸው፡፡
ለዚህም ማሳያ ከዓለም ባንክ ማለትም ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር (International Development Association) የሚወሰደው ብድር 0.75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ውጭ ምንም ወለድ ክፍያ የሌለውና በረዥም የክፍያ ጊዜ ማለትም በ38 ዓመት የሚከፈል ነው። እነዚህን መሰል ብድሮች ከአጠቃላ የውጭ ብድር 42 በመቶ ድርሻ ያላቸውና የብድር ጫና የማያስከትሉ ናቸው።
2.መንግሥት የሀገሪቱን የዕዳ ክፍያ ጫና ለመቀነስ የተለያዩ የብድር ሽግሽግና ማቅለያ ስምምነቶችን ኃላፊነት በተሞላ መልኩ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ባለፉት ዓመታትም የተለያዩ የብድር ሽግሽጎች የተደረጉ ሲሆን ከ2023 ጀምሮ ደግሞ በG-20 Common Framework የዕዳ ሽግሽግ ተጠቃሚ በመሆን ከአበዳሪዎችና ጋር ስኬታም ድርድር በማድረግ የዕዳ ክፍያ ጫና እንዲቀንስ እየተሰራበት ይገኛል።
በተጨማሪም ጋዜጣው ያወጣው ትንተና አውዱን ያልጠበቀ እና የተሳሳተ አረዳድ የሚሰጥ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአንድ አገር የብድር ጫና መለኪያዎች የውጭ ብድር መጠን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጥመርታ፣ የውጭ ብድር መጠን ከወጭ ንግድ ገቢ ጥመርታ፣ ዓመታዊ የውጭ ብድር ክፍያ ከወጭ ንግድ ገቢ ጥመርታ እና ዓመታዊ የውጭ ብድር ክፍያ ከዓመታዊ የመንግሥት ገቢ ጥመርታ ናቸው፡፡ የአገሪቱን በእነዚህ መለኪያዎች መሠረት ያለችበትን የዕዳ ሁኔታ ለማሻሻል ከላይ እንደተገለጸው ከአበዳሪዎች ጋር የተሳካ ድርድር እየተደረገ በመሆኑ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የአገሪቱ የብድር ሁኔታ ወደ ተሻለ ሁኔታ የሚሸጋገር ይሆናል፡፡
የነፍስ ወከፍ ዕዳ እንደ መመዘኛ ሪፖርቱ እንደሚጠቅሰው የፐብሊክ ፋይናንስ አቅምን ለመመዘን የማያስችል፣ የዕዳ ጫናን የማያመላክትና ዘገባውን ስሜት ቀስቃሽ ከማድረግ ውጪ አግባብነት የሌለው ነው።
የሀገር ውስጥ ብድር ክምችትን በተመለከት እ.ኤ.አ በ2024 መጨረሻ የሀገር ውስጥ ብድር 2.3 ትሪሊየን ብር ነው።
የሀገሪቱን ብድር በሚመለከት የሚሰራጩ መረጃዎች ለህብረትሰቡ ትክክለኛ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ፣ የገበያውን እንቅስቃሴና ምላሽ እንዲዛባ በማያደርጉ መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው እሙን ነው።
ስለሆነም የተለያዩ መረጃዎችና መሰል ትንተናዎች ሲዘጋጁ እንደአግባብነቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሙያዎችን ማማከር፣ ኦፊሻል መረጃዎችን መጠየቅና ሃሳብን መቀብል እንደአማራጭ እንዲወሰዱ እንመክራለን።
የገንዘብ ሚኒስቴር
ምላሽ ይስጡ