የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጊዜያዊነት የተቀመጡትን የጠቅላይ ምክር ቤቱን አመራር ማለትም መጅሊስ እና ኡለሞች በህጋዊ መልክ እና በህዝቡ ፍላጎት መሰረት ምርጫ ላካሂድ ነው ብሏል፡፡
በውክልና ሲመራ የነበረውን መጅሊስ በህብረተሰቡ ፍቃድ እና እውቅና መሰረት ለማድረግ በመላው ሀገሪቱ ባሉ መስጂዶች ጊዜያዊ የምርጫ ጣቢያ በማዘጋጀት ምርጫውን ለማከናወን እንደታቀደ ምክር ቤቱ በግዜያዊነት ያቋቋመው ምርጫ ቦርድ ዋና ጸሀፊ መሀመድ ጠይን ተናግረዋል፡፡
ምርጫውን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ቅድመ ምዝገባ ስራ መጀመሩ ተገልጾል፡፡ አክለውም በሀገሪቷ ባሉ አራቱም አቀጣጫዎች የእስልምና ተወካዮች ምርጫውን ፍትሃዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዲቻል መመሪያ ማስረከባቸውን ዋና ጸሃፊው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሚያካሂደው ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ምርጫው የሚከናወንበት ሶፍትዌር መዘጋጀቱን በምክር ቤቱ የቴክኖሎጂ ቡድን መሪ ፋይሰል መሀመድ ገልጸዋል፡፡
ይህ ዘመናዊ አሰራር መሰረተ ልማት በተሟላባቸው ከተማ እና ክልል ከተሞች ምርጫውን በቴክኖሎጂ በማገዝ አላግባብ ወጪ እና የሰዓት ብክነትን ለመቆጣጠር ብሎም የምርጫው ሂደት በተጠናቀቀበት ጊዜ እና ሰዓት ውጤቱን በአፋጣኝ ለማሳወቅ እንደሚረዳ አቶ ፈይሰል ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የቦርዱ አባላትና አመራሮች ፣ የመጅሊሱ አመራሮች ፣ ዑለሞች የማህበረሰብ መሪዎችና በየደረጃው ያሉ የምርጫ አስፈጻሚ አካላት በሀላፊነት ምርጫው እንዲከናወን የገቡትን ቃለ መሀላ ሳይዘነጉ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ምርጫ ለጽኑ ተቋም በሚል መሪ ቃል በመጪው ሐምሌ ወር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ