ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሚዲያ አገልግሎት በተሰኘ የዜና ማሰራጫ እንደ ሰበር ዜና የተላለፈ መልእክት “በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውስጥ አካውንት ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ መዘረፉ ተገለፀ” በማለት ባንካችን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደተዘረፈ፣ ዘራፊዎቹ እንዳልተያዙ እና ባንካችንም ጉዳዩን አድበስብሶ እንዳለፈው የሚገልጽ የሐሰት ዜና ስለተዘገበ በጉዳዩ ላይ አጭር መግለጫ ለመስጠት ተገድደናል።
ከላይ የተጠቀሰው ሚዲያ እና ሌሎችም ይህንኑ ሚዲያ ያጣቀሱ ሚዲያዎች ከባንካችን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደተዘረፈ የሚገልጽ ዜና ቢዘግቡም፣ እውነታው ግን፡-
➢ በሚዲያዎቹ ከተዘገበው በተቃራኒ ከባንካችን ምንም የተዘረፈ ገንዘብ አለመኖሩን፣ ይልቁንም ከፍተኛ ገንዘብ ለመዝረፍ የተደረገ ሙከራ መሆኑን፣
➢ ባንካችን ሙከራው በተደረገ በጥቂት ደቂቃዎች ዉስጥ በጠንካራው የውስጥ ቁጥጥር ስርአታችን አጠራጣሪ ግብይት መፈፀሙን ስለደረሰበት ምንም ዓይነት ገንዘብ ወጪ ሳይደረግ ሙከራው ወዲያውኑ እንዲከሽፍ መደረጉን፣
➢ ሙከራው በጥቂት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ባሰቡ ተጠርጣሪዎች የተፈፀመ እንጂ የባንካችንን ሲስተም ተላልፎ የተፈፀመ ጥቃት አለመሆኑን፣
➢ ባንካችን ሙከራ የተደረገበትን ገንዘብ ባለው ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት አማካኝነት ከጥቃት ከተከላከለ በኋላ ጉዳዩን ለሚመለከተው የሕግ አካል በማሳወቅ ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉና የምርመራ ስራውም ተጠናክሮ እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑን፣
➢ በማጠቃለያም ባንካችን እንደማንኛውም የፋይናንስ ተቋም በተለይም እንደ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋምነቱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት አስበው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ኢላማ መሆኑ እሙን ቢሆንም እንዲህ አይነቱን ሕገ ወጥ ተግባር ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓትና የዘመነ ሲስተም ያለው ለመሆኑ ይህ የሙከራ ድርጊት መክሸፉ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅትም ጉዳዩ በሕግ አካላት ተይዞ ጥብቅ ክትትል እየተደረገበት የሚገኝ እና የምርመራ ሂደቱም ያልተጠናቀቀ መሆኑን እያሳወቅን በቀጣይ የሕግ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ዝርዝር መረጃውን የምናሳውቅ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ