በ2021 የቦክስ ጓንቱን የሰቀለው አንጋፋው ቡጢኛ ማኒ ፓኪው ከስፖርቱ ራሱን አግልሎ በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተጠምዶ በሀገሩ ፊሊፒንስ ከ2016-22 በከንቲባነት ያገለገለ ሲሆን በ2022 ደግሞ በሀገሩ ፊሊፒንስ ለፕሬዚዳንት ለመመረጥ ራሱን እጩ አድርጎ መቅረቡ አይዘነጋም።
በፈጣን ስንዘራዎቹ እና ናላ አዙሮ በሚዘርረው ቡጢ የሚታወቀው የ46 አመቱ ቡጢኛ ማኒ ፓኪው ጓንቱን ከሰቀለበት አውርዶ ከባሪዮስ ጋር እንደሚፋለም ከ8 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ባሉት የማህበራዊ ትስስር ገፆ ላይ ይፋ አድርጓል።
ማኒ ፓኪው በWBC የቦክስ ማህበር ላይ በWelter weight division ወይም ከ71-78 ኪሎ የሚመዝኑ ተፋላሚዎች የሚፋለሙበት እርከን ላይ ከቀበቶ አሸናፊው ሜክሲኮአዊው ቡጢኛ ማሪዮ ባሪዮስ ጋር ቀበቶውን ለግሉ ለማድረግ ነው ፍልሚያውን የሚያከናውነው።
ፍልሚያው በቀጣዩ ወር በፈረንጆቹ ሰኔ 19 በአሜሪካ ላስ ቬጋስ MGM ግራንድ ላይ የሚከናወን ይሆናል። ፓኪው አስደናቂ በነበረው የቦክስ ህይወቱ ወደ 72 የቦክስ ፍልሚያዎችን ያከናወነ ሲሆን 62ቱን በማሸነፍ ፤ 8 ጊዜ በመሸነፍ እንዲሁም ሁለት ጊዜ ፍልሚያዎቹን በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ በቦክሱ አለም ትልቅ ታሪክ ከፃፉ ቡጢኞች መካከል አንዱ ነው።
በ2015 የምዕተ አመቱ ምርጡ ፍልሚያ የሚል ስም የተሰጠው እና ማኒ ፓኪው ከ ፍሎይድ ሜይዌዘር ጋር ያደረጉት ፍልሚያ ከቦክሱ አፍቃሪያን ትውስታ ማህደር ውስጥ አይጠፋም። ይህ ፍልሚያ በጊዜው 600 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘ ሲሆን በቦክስ ታሪክ ከዚ ፍልሚያ በላይ ገቢ ያስገኘ የቦክስ ፍልሚያ አልተገኘም።
ማኒ ፓኪው በ8 የተለያዩ የክብደት እርከኖች የአለም ሻምፒዮናዎችን ማሳካት የቻለ እንዲሁም በ2019 በ40 አመቱ የWelterweight የቀበቶ ክብርን የግሉ ማድረግ የቻለ በእድሜ አንጋፋ በሚል አዲስ ታሪክ የፃፈ ብቸኛው ቡጢኛ ነው።
በሚካኤል ደጀኔ

ምላሽ ይስጡ