በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደረውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ያለበትን የኑሮ ጫና ለማቅለል በመንግስት የተቋቋሙት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ከ200 ማለፋቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
የሰንበት ገበያዎች የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና የተረጋጋ ገበያ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እየተወጡ እንደሆነ የሚናገሩት የቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ፤ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ 216 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በበጀት አመቱ ከ16 በላይ የሚሆኑ የሰንበት ገበያዎች በኮሊደር ልማቱ ምክንያት ባይቀነሱ በመዲናዋ የሚገኙ የሰንበት ገበያዎች ከ240 ያልፉ እንደነበር ሃላፊው ገልጸው፤ በአቃቂ፤ ገላን ጉራ፤ ጃርሶና ቦሌ አካባቢ የትራፊክ መጨናነቅ በማይፈጥር መልኩ ተጨማሪ የሰንበት ገበያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎች እየገቡባቸው ባሉ አዳዲስ መንደሮች ላይ ተጨማሪ 33 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ለማስጀመር ቢሮው በዝግጅት ላይ እንደሆነ ሃላፊው አንስተው፤ ለተወሰነ ጊዜ ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው ባሉ የሰንበት ገበያዎች ግብይት እንዲያከናወኑ ጠይቀዋል፡፡
ተገልጋዮች የሚኖራቸውን ማንኛውም ጥያቄ ማስተናገድ የሚችሉ የስልክ መስመሮች በሰንት ገበያዎቹ ስፍራ በመኖራቸውና በአቅራቢያ ለሚገኙ ተቆጣጣሪዎች ጥቆማዎችን ማቅረብ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ