ዘንድሮ ከሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 8/2017 ዓ/ም የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና 608 ሺህ ተማሪዎች እንደሚወስዱ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
አገልግሎቱ የ2017 ዓ/ም የ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስጠት ዓመቱን በሙሉ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጻል፡፡ ይሁን እንጅ የፈተናውን ሒደት የሚያውኩ ተማሪዎች ካሉ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ነው የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ባይሳ ለመናኸሪያ ሬዲዮ የተናገሩት፡፡
ካለፉት 3 አመታት ልምድ በመውሰድ ተፈታኞችን በመለየት እና ተገቢነትን በማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸው፤ እስካሁን ባለው መረጃ 68 ሺህ ለሚሆኑ ተፈታኞች መፈተኛ ካርድ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡
ተማሪዎች ፈተናው በሚሰጥበት ጊዜ ከስነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት እንዳይፈጽሙ አስቀድሞ በትምህርት ቤቶች አማካኝነት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን የገለጹት አቶ ተፈራ፤ ነገር ግን የፈተና ሂደቱን ለማወክ የሚሞክሩ ካሉ የትምህርት ማስረጃቸውን እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጸዋል፡፡
ፈተናው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተጨማሪ በሌሎች የትምህርት ማዕከላት እንደሚሰጥ ነው የገለጹት፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር የፈተና መስጫ ጣቢያ መሆን የሚችሉት የመንግስት ተቋማት ብቻ እንደሆነ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ አገልግሎቱ አዲስ መስፈርት በማውጣት ሌሎች የትምህር ተቋማት መስፈርቱን አሟልተው ከተገኙ ማስፈተን እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
የ12ተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በበይነ መረብና በወረቀት እንደሚሰጥ መገለጹ ይታወቃል፡፡
__
ምላሽ ይስጡ