የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራሰ ገዝ የመንግስት ተቋም ከሆነ በኋላ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ተደራሽነቱን ለማስፋት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ቢገኝም በበይነ መረብ ማስተማር እጀምራለሁ ብሎ የነበረውን የምልክት ቋንቋ ትምህርት በግብዓት ማነስ ፣በባለሙያ እጥረት፣በቴክኒካል ጉዳይ ፣በኢንተርኔት አለመደራጀት እና ካሊኩረም ባለመቀረጹ ምክንያት መጀመር አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ እና መስማት የተሳናቸው ባህል ዘርፍ መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር እያሱ ሀይሉ እንደተናገሩት የምልክት ቋንቋ በተቋሙ በመደበኛ እና ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ የማስተማር ሂደቱን ሲከናውን የቆየ ቢሆንም ከዕለት ተዕለት የህብረተሰቡ በዘርፉ የመማር ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ በበይነ መረብ ፣ በክረምት፣ እና በማታ መርሀ-ግብር ለመስጠት ያቀደ ቢሆንም በእቅዱ ልክ አለማሳካቱን ገልጸዋል፡፡
ቋንቋው በእጅ እንቅስቃሴ እይታ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ምስል መቅረጽ አስፈላጊ በመሆኑ ለቀረጻ የሚመጥን ቦታ እና ቁሳቁሶች አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ባለመኖር ፣በዘርፉ ለመስራት ፍቃደኛ የሆኑ መምህራን ውስንነት ፣ ለመማር ማስተማሩ ሂደት የሚመጥን ካሪኩለም ለመቅረጽ የዘርፉ ባለሙያዎች እጥረት ፣ተማሪውን እና አስተማሪው የሚገናኝበት አማራጭ ባለመዘጋጀቱ ትምህርቱን ለመስጠት ተግዳሮት እንደሆነባቸው አንስተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው እየሄደ ባለው የለውጥ አቅጣጫ አብረው እንዲቀጥሉ ፍቃድ ከተሰጣቸው መርሃ-ግብሮች አንዱ የምልክት ቋንቋ እና ማስተርጎም ትምህርት ሲሆን በዚህ ጉዳይ የትምህርት ሚንስቴር ጣልቃ ገብነት ባለመኖሩ በታቀደው ልክ እንዳይሄድ ያደረገዉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሆኖም ዩኒቨርሲቲው ያጋጠመውን ተግዳሮት ለመቅረፍ ድጋፍ ከመንግስትም ሆነ ከባለድርሻ አካላት እንደሚሻ የገለጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ እና መስማት የተሳናቸው ባህል ዘርፍ መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር እያሱ ሀይሉ ናቸው፡፡
__
ምላሽ ይስጡ