ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋና ምቹ የሆነ አገልግሎትን ለመስጠትና እንደ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በቂ የህግ ጥበቃ ለማድረግ የኢ- ሰርቪስ አገልግሎት አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው ሞሲሳ ገልፀዋል።
የኢ-ሰርቪስ አገልግሎቱን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ ተደርጎ እንደሚጀመር የጠቆሙት አቶ እንዳለው፣ አሁን ላይ ዘመኑ የቴክኖሎጅ እንደመሆኑ መጠን የተገልጋዮችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የተሳለጠ አገልግሎትን ለመስጠት ዘመኑ ከሚዋጀው የቴክኖሎጅ ውጤት ጋር መራመድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ባለስልጣኑ የንግድ ምልክት፣ ፓተንት፣ የቅጅ ተዛማጅ መብቶችንና ሌሎችንም ስራዎችን ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከስነ- ጥበብና ኪነ- ጥበብ ሰዎች ጋርም በኢ- ሰርቪስ ለመገናኘት ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ እንዳለው ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሄራዊ ኤሌክትሮኒክ የመንግስት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሚራጅ ዘኪይ፣ በሃገሪቱ የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማፋጠንና ቀልጣፋ ለማድረግ የኢ- አገልግሎት በሁሉም ተቋማት እንዲጀመር ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ገልፀዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡ ምቹና ቀልጣፋ ሲሆን የሃገር ኢኮኖሚም እንደሚያድግና የአለም ተሞክሮም እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ ሚራጅ፣ ሃገራችንንም በቴክኖሎጅ አስተሳስሮ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በቀጣይ በጋራ እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ