በተለያዩ ጊዜያት ሀገሪቷን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ ጎብኚዎች እንዳሉ ቢታወቅም በአብዛኛው በሚባል ደረጃ የጎብኚዎች ቀጥር እየተቀመጠ ያለው በግምት ስለመሆኑ ያስታወቀው የኢትዮጵያ አሰጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ነው፡፡
የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ክብሮም ተስፋዬ ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገራት እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ያሏት ቢሆንም የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን መነሻ በማድረግ እና የጎብኚዎች ቁጥርን በማስቀመጥ ውስጥ ትክክለኛ አለመሆኑን እና ግምታዊ የሆኑ ቁጥሮችም ማስቀመጥ እየተለመደ መጥቷል ብለዋል፡፡በዚህም ሀገሪቱ የራሷ የምትለው የመረጃ ቋት አለመኖርን ተከትሎ የጎብኚዎች ቁጥር በግምት እንዲቀመጥ እያደረገው ስለመምጣቱም አመላክተዋል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም ይህ አይነቱ ልማድ ጎልቶ እንዲታይ እያደረጋቸው ካሉ ምክንያቶች ውስጥ የተደራጀ የመረጃ ቋት አለመኖር ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በማህበሩ ሃሳብ የማይስማማው ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ ቁጥሮቹ በዘፈቀ ሳይሆን ሳይንሳዊ የሆነ ቀመርን የሚከተሉ ናቸው ብሏል፡፡ የአቆጣጠር ስልቶች በርካታ ቢሆኑም ሳይንሳዊ የሆነ ቀመርን የሚከተሉ ናቸው ያሉት በቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው ናቸው፡፡
ቱሪስቶች የሚይዙት ሆቴል ፤የሚመጡባቸው ተሽከርካሪዎች እና መሰል ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቁጥሮች ይቀመጣሉ ብለዋል፡፡
አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለፈው አመት የጎብኚዎችን ቁጥር፤የገቢ መጠን እና መሰል ነገሮችን መመዝገብ የሚቻልበት TOURISM SATELLITE ACCOUNT የተሰኘ የአሰራር ስርዓትን ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም እድገት መኖር ጠቀሜታ እንዳለው የሚገለጽ ሲሆን አንዱ እና ዋነኛው ገቢን ማሳደግ እና መዳረሻ ስፍራዎችን ማበራከት እንደሆነ ይታመናል፡፡
__
ምላሽ ይስጡ