በተመረጡ 6 ዘርፎች ላይ 5ኛው የጣፋጭ ህይወት የምስጋና መርሃ-ግብር ሊካሄድ መሆኑን ጣፋጭ ህይወት ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
በየአመቱ እየተከናወነ ያለዉ የጣፋጭ ህይወት የምስጋና መርሃ-ግብር ዘንድሮ በስራ ፈጠራ፣ በበጎ አድራጎት፣ ማህበራዊ ሚድያውን ለመልካም ተግባር በመጠቀም እና በሌሎችም ተጨማሪ ሶስት ዘርፎች በአጠቃላይ በስድስት ዘርፍ የምስጋና መርሃ-ግብሩ እንደሚከናወን የጣፋጭ ህይወት ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሰለሞን አይዳኝ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
የምስጋና መርሃ-ግብሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን፣ የህክምና ባለሙያዎችንና ሌሎችንም የሚያካትት ሲሆን በተጨማሪም ቤተሰብ፣ ሹፌሮችና መምህራንን የመሳሰሉ ዘርፎችም የሚመሰገኑበት መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ገልጸዋል።
በመጪው ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል የተባለው የምስጋና መርሃግብሩ ፡ እጩዎችን ማህበረሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ጥቆማ በማድረግ ላይ ይገኛል ሲሉ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። እስከ ግንቦት 30 ቀን ጥቆማዎች ከተሰባሰቡ በኋላ በቦርድ አማካኝነት ፍትሃዊ ምርጫ እንደሚካሄድም አክለዉ ገልጸዋል፡፡
መርሃ-ግብሩ በዋናነት የምስጋና ባህል እንዲያድግ ጥረት የሚያደርግ ነው ያሉት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ዘንድሮ አዲስ የምስጋና ዘርፍ ባይካተትበትም በቀጣይነት ባህሉን የማዳበር ስራው ግን እየተካሄደ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
አቶ ሰለሞን አክለውም የምስጋና መርሃ-ግብሩ የት እንደሚሰናዳ በቅርቡ መግለጫ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ምላሽ ይስጡ