አንድ ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅናውን ካጣ በኋላ የሚያደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ኢ-ህገ መንግስታዊ ይሆናል ሲሉ የህግና የፌዴራሊዚም ባለሙያዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰውነቱን ያጣው ህወኃት በቀጣይ የሚያደርጋቸው ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ኢ-ህገ መንግስታዊ ይሆናል ያሉት የዓለም አቀፍ ፖለቲካና ፌዴራሊዚም ባለሙያ ዶክተር ኃይለኢየሱስ ታየ፤ ነገር ግን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመወስድ ክስ የመመስረት መብቱ የተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
የፓርቲው አባላት ማንኛውንም የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ እንደማይችሉ በማመላከት በተለይም ከሃብትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተገናኘው በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ተፈፃሚ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎች የሀገሪቷን ህግና ስርዓት አክብረው መንቀሳቀስ አለባቸው ሲሉም አፅኖት ሰጥተዋል፡፡
የፌዴራሊዚምና የህግ ባለሙያው አቶ አቤኔዘር ጥሩአየው በበኩላቸው በፓርቲው ስም ያሉ ሀብቶች ላይ ማጣራት እንደሚደረግና በህዝብ ስም የነበሩ ህዝባዊ ድርጅቶች ግን ባሉበት እንዲቀጥሉ ህጉ እንደሚፈቅድ አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ በተለይም ፓርቲው በክልሉ ያለውን ተቀባይነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የቀድሞ ታጋዮችን ዳግም በመጥራት ማስተካከያዎችን ይወስዳል የሚል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ባለሙያዎቹ ፓርቲዎች ሠላማዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር መስራት እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ