አቶ ጌታቸው ረዳ ያወጡት መረጃ መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን የወንጀል ድርጊት ጣልቃ ገብቶ እንዲከታተል የሚያስገድድ ነው ሲሉ ጣቢያችን ሃሳባቸውን ያሳፈሩ የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የህግ ባለሙያው አቶ መታገስ ውለታው አቶ ጌታቸው ረዳ ያጋሩት መረጃ ለፌደራል መንግስት ወሳኝ ጥቆማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ስለተፈጸመው የማዕድን እና የባንክ ዘረፋ በግልጽ ድርጊቱን የፈጸሙትን ሰዎች ስም ሳይቀር መናገራቸው ለፍትህ አካላት ክትትልና ፍትህን የማስፈን ስራ እንደ ጠቃሚ መረጃ ታይቶ ክትትል መደረግ አለበት ብለዋል።
ከህግ አንጻር የማህበረሰብና የግለሰቦች መረጃ ጠቃሚ ተደርጎ ይወሰዳል ያሉት ባለሙያው፤ አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ በቅርበት ድርጊቱ ሲፈጸም የነበሩና የአይን እማኝ መሆናቸውን ያመኑ ምስክር በመሆናቸው ለፌደራል ፖሊስና በጥቅሉ ለፍትህ አካላት ቀጣይ የምርመራ ሂደት ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ የተናገሯቸው መረጃዎች እውነት ከሆኑ የወንጀል ድርጊቶች መሆናቸው በህግ የተቀመጠ ነው የሚሉት አቶ መታገስ፤ የፌደራል መንግስቱ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ጣልቃ ገብቶ ፍትህን የማስፈን መብት አለው ብለዋል።
ብዙዎች በሚመለከቱት መገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው የሰጡት መረጃ ፌደራል መንግስቱ ትኩረት ሰጥቶት ካልተከታተለው በመንግስትም ላይ ተጠያቂነትን ያመጣል ሲሉ ሃሳባቸውን ያሳፈሩት ደግሞ ሌላኛው ጠበቃና የህግ ባለሙያ አቶ ጌቱ አስናቀው ናቸው።
የአቶ ጌታቸው ረዳን መረጃና ጥቆማ ፌደራል ፖሊስም ሆነ አቃቢ ህግ በቂ ክትትል ያደርግበታል ተብሎ ከህግ አካሄድ አንጻር ይጠበቃል ሲሉ አክለዋል።
በሌሎችም ሀገራት ልምድ መሰል ሀገራዊ ከባድ የወንጀል ድርጊቶች ሲፈጸሙ እማኝ የነበሩ ግለሰቦችና የባለስልጣናት መረጃ ጠቃሚ ሲሆን ይስተዋላል ያሉት የህግ ባለሙያው፤ የትግራይ ክልልን ሰላም በማስፈንና ወንጀልን በመቀነስ ሂደት እንዲህ ያሉት ይፋዊ ጥቆማዎች ለፌደራል መንግስቱ ወንጀልን የመከላከል ሂደት አጋዥ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት፤ የአሁኑ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል ተከናውነዋል ስላሉት የወንጀል ድርጊቶች ሰሞኑን በፋና ቴሌቪዥን ቀርበው መናገራቸው ይታወሳል።
ምላሽ ይስጡ