ግንቦት 4 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። በፎረሙ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና ሌሎች ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።
የቢዝነስ ፎረሙ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በአጋር የልማት ድርጅቶች የተዘጋጀ ነው። በተጨማሪም በፎረሙ የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ታዋቂ ኩባንያዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ አማካሪዎች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ታድመዋል።
ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄደው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ የቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ተቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት የመፍጠር አላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል።
አዳዲስ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ማሳየት እና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማሳወቅ ከፎረሙ ዓላማዎች መካከል ይገኙበታል።
ዛሬና ነገ በሚካሄደው ፎረም በርካታ የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ታዋቂ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ።
(ENA)
ምላሽ ይስጡ