በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የውሃ ሀይል ማመንጫ ግድቦች መጪውን የክረምት ወቅት ተከትሎ ሞልተው የማስተንፈስ ስራ ከመከናወኑ አስቀድሞ ለማህበረሰቡ የጥንቃቄ መልዕክት እንዲደርስ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
በተወሰኑ የሀይል ማመንጫ ግድቦች በተለያዩ ጊዜያት ዝናብ የሚያገኙ በመሆኑ ግድቦቹ የሚሞሉበትና የማስተንፈስ ስራም እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ተናግረዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ግድቦች የሚሞሉት የክረምት ወቅት ካለፈ በኋላ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ እንደ ተከዜ እና የገናሌ ዳዋ 3 ግድቦች ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በዓመት ሁለት ጊዜ ዝናብ የሚያገኙ በመሆናቸው የሚሞሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል፡፡
በተለይም በጥገና ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ ግድቦች ሞልተው በማህበረሰቡ ላይ የጎርፍ አደጋ እንዳያስከትሉ ተቋሙን ጨምሮ ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የሞሉ ግድቦችን የማስተንፈስ ስራ የሚሰራው በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውሳኔ መሰረት መሆኑን በመግለፅ በዚህም ማህበረሰቡ የጥንቃቄ መልእክት እንዲደርሰውና ከአካባቢው እንዲለቅ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የክረምት ወቅትን ተከትሎ ሞልተው በማህበረሰቡ ላይ ስጋት የሚፈጥሩ ግድቦች ከተስተዋሉ በመከታተል ለሚመከተው አካል የሚያሳውቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ