ይህ የተገለጸዉ የሚዲያ ባለሙያዎች ትላንት የመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎትን እንዲጎበኙ በተደረገበት ወቅት ነዉ።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በማጣመር በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የታገዘ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ አይነቱ አሰራር ዜጎች የተለያዩ የፌደራል ተቋማትን አገልግሎትን በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ያስችላል ሲሉ ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ናቸው።
የገቢዎች፣የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስርና የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ 12 ተቋማትን እና ከ46 በላይ ዋና ዋና አገልግሎት በአንድ ማእከል ማግኘት የሚያስችለው ፕሮጀክት በይፋ ወደስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ተጠቃሚዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ አንስተው፤ ከተቋም ወደ ተቋም የሚኖር እንግልት ብሎም የጊዜና የገንዘብ ብክነትን በማስቀረት አገልግሎትን በአንድ ተቋም በኔትዎርክ ያስተሳሰረ መሆኑን አመላክተዋል።
ይህም ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ስራዎችን የሚያሰቀር በመሆኑ ወደፊት በሚኖረው የማስፋፋት ስራም በርካታ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ጠቁመዋል ።
የዳታ ሴንተሩ አስተማማኝ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴታው ከሌሎች የአለም ሃገራት ልምድ የተወሰደበትና በቴክኖሎጂ ግብዓቶች የተደራጀ በመሆኑ ምንም አይነት የአገልግሎት መቋረጥ ስጋት በመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት እንደማይኖር አስረድተዋል።
በቀጣይም በክልሎች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የመሶብ አገልግሎት ተቋማትን ለመክፈት በቅድ መያዙንና አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ