የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የህንጻ ግንባታን በ4 መቶ ሚሊዮን ብር ለማከናወን በ2009 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተጣለ ሲሆን በ2010 ዓ.ም የግንባታ ስራው እንደሚጀመርና በሶስት አመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡ ግንባታው የአቪዬሽኑን ዋና መስሪያ ቤት እንዲሁም የአቪዬሽን ሙዚየም ግንባታን የሚያጠቃልል እንደሆነም ሲገለጽ ቆይቷል።
የዚህን የህንጻ ግንባታ በተለመከተ ተቋሙ የ9 ወር እቅድ አፈጻጸም ለመሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በተገኙበት ሪፖርት ሲያቀርብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወ/ሮ ታለፍ ፍታወርቅ፣ የግንባታ ስራው ከተጀመር በርካታ አመታትን ያስቆጠረ ስለሆነ የግንባታ ሂደቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠይቀዋል፡፡
አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ ባይገልጹም ግንባታውን በተመለከተ ምላሽ የሠጡት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ፣ ግንባታውን በዋናነት የሚከታተለው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እንደሆነ ተናግረዋል።
የግንባታ ተቋራጭ በተደጋጋሚ በሚያጋጥመዉ ችግር ምክንያት እስካሁን ሲጓተት እንደቆየ ገልጸዋል፡፡ ለብዙ ጊዜ ቆሞ የቆየውን ይህ የግንባታ ስራ በመልሶ ግንባታ ማስጀመር ለሃገር ውስጥ ተቋራጮች ተሰጥቶ እንደነበርና በ2017 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም አሁንም ተቋራጩ አጋጠመኝ ባለው ችግር ምክንያት እስከቀጣይ አመት ጥር ወር 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲጠናቀቅ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ግፊት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግንባታ ስራዉ ቢጠናቀቅ ለዘርፉ አዲስ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ቢታመንም ላለፉት 8 ዓመታት ስራዉ በመጓተቱ ምክንያት የቆመውን ህንጻ ሰርቶ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡
ምላሽ ይስጡ