ወደ ተለያዩ ሀገራት አንዳንድ ምርቶች ሲላኩ በጥራት መጓደል እንዲሁም በህገወጥ ግብይት ምክንያት በሚፈለገው ልክ ገቢ እንዳይገኝ ተግዳሮት መሆኑ ይገለፃል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ሀገራት አምርታ ከምትሸጣቸው ምርቶች መካከል ጫት ተጠቃሹ ነው፡፡ የጫት ምርት ወደውጭ ሀገራት ሲላክ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን እና በህገወጥ መንገድ እንዳይወጣ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ነገር ግን ምርቱ በህገወጥ መንገድ ለመውጣት ተጋላጭ እንደሆነ እና በዚህም የጥራት ችግር እንዲፈጠር ምክንያት በመሆኑ ይህንን ለመፍታት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ነጋዴዎች ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርት በማስቀመጥ በክልሎች ተግባራዊ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ለጣቢያችን የገለፁት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ናቸው፡፡
ልክ እንደ ቡና እና ሌሎች ምርቶች ጫት ለሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢን ከማስገኘት አኳያ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ሀገራትም ምርቶች ሲላክላቸው በቀዳሚነት የሚያስቀምጡት መስፈርት ጥራት እንደመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የምርት ጥራት ችግር እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆነው ህገወጥ ግብይት በመሆኑ በክልሎች የሚገኙ የማይታወቁ ኬላዎችን በማስነሳት፣ ግበረ ሃይሎችን በማቋቋም ከክልል መንግስታት ጋር በመቀናጀት የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አንደ ሀገር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች የጥራት ጉዳይ ላይ እንዲሁም ህገወጥ የንግድ ስርዓትን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ