የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን እየተደረገ ላለው ጥረት ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን ማድረግ እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
የደቡብ ሱዳን ባለድርሻ አካላት ለሰላም ስምምነቱ መከበር በቁርጠኝነት እንዲሰሩም አሳስበዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ጋር በጋራ በመሆን ወደ ደቡብ ሱዳን በማቅናት ሚያዚያ 27 እና 28 ቀን 2017 ዓ.ም ከሀገሪቷ ባለስልጣናትና ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ተቋማት የውይይቱን ውጤቶች እና ቀጣይ እርምጃዎች አስመልክቶም የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። ምክክሩ በደቡብ ሱዳን የፖለቲካ እና የደህንነት ሁኔታ እንዲሁም የሰላም ሂደቱ ያለበትን ደረጃ የተመለከተ ነው።ጉብኝቱ ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ በ2018 በተፈረመው አዲሱ የግጭት ማስቆም እና የሰላም ስምምነት አማካኝነት በሽግግር ውስጥ እያለፈች በምትገኝበት ወሳኝ ወቅት የተደረገ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
በጁባ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋርም ውይይት ተደርጓል። የጋራ መግለጫው ውይይቱ ያተኮረባቸውን ነጥቦች አስቀምጧል።በከፍተኛ ጥረት የተገኘውን የሰላም ስምምነት ውጤቶች ማስጠበቅ፣ ሁሉን አሳታፊ ብሄራዊ ምክክር ማድረግ እና መግባባት ላይ መድረስ እንዲሁም በጊዜ ገደብ የሚፈጸም፣ ተአማኒነት ያለውና ግልጽ የሆነ የሽግግር ፍኖተ ካርታን መደገፍ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የአስተዳደር ተቋማትን አቅም ማጠናከርም የምክክሩ ሌላኛው ትኩረት ነበር።
በተጨማሪም የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ከቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ ከአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ እና የተለያዩ ሀገራትን ካቀፈው የትሮይካ ስብስብ ተወካዮች ጋር የደቡብ ሱዳንን የሽግግር ሂደት በአንድ ወጥ አካሄድ መምራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ኢጋድ ሰላም፣ መረጋጋት እና ሁሉን አቀፍ አስተዳደር ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እና ቀጣናዊ ትስስር ጽኑ መሰረትን የሚጥሉ ጉዳዮች እንደሆኑ በመግለጫው ላይ አመልክተዋል።
የጋራ መተማመን፣ ብሄራዊ የህዝብ አንድነት እና የጋራ ትብብር፣ የፖለቲካ እና የሲቪክ ምህዳሩን ማክበር፣ ለውይይት እና ለመግባባት ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ ከደቡብ ሱዳን መንግስት፣ ከቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን የሀገሪቷ ሰላም ዘላቂ እንዲሆን እና የሰላም ስምምነቱ ቁልፍ ጉዳዮች እንዲጠበቁ በሙሉ ቁርጠኝነት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን መጻኢ ጊዜ አንድነት የሰፈነበት፣ በፈተናዎች የማይበገር እና ብልጽግና የተረጋገጠበት እንዲሆን ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ነው በመግለጫው ያመለከቱት።
(ENA)

ምላሽ ይስጡ