ሙሉ መግለጫው ከታች ተያይዟል
ጉዳዩ፡ ማህበሩ በቅርቡ ያካሄደው ጉባኤን ይመለከታል
የትግራይ ልማት ማህበር (ትልማ) በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት በመዝገብ ቁጥር 0462 በተቋማችን የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ይታወቃል። በዚሁ መሰረትም ትልማ 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመቀሌ ከተማ ከሚያዝያ 17 እስከ 19/2017 ዓ.ም እንደሚያካሂድ በመግለፅ ተቋማችን በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ጥሪ ባቀረበው መሰረት የተቋማችን ሁለት ተወካዮች በጉባኤው ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል።
በጉባኤው ላይም ተቋማችን በመወከል የተገኙት አመራሮች ጉባኤው ትልማ ተጠናክሮ በቀጣይ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት የበለጠ የሚያረጋግጥ ሥራ እንዲያከናውን የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠርበትና አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት እንዲሆን ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በጉባኤው ውይይቶች ወቅት ለሚነሱ ድጋፍ በሚሹ
ጉዳዮች ላይ ህግንና አሰራር መሰረት በማድረግ ገንቢ ሃሳቦችን አጋርቷል።
ይህ ጉባኤ ከተሳታፊዎች አጠራር ጀምሮ መሰረታዊ መስፈርቶችን ያላሟላ በመሆኑ መካሄድ የሌለበትና መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች ያሉ መሆኑ ለትልማ አመራሮችና ለጉባኤው ሃሳብ የቀረበ ቢሆንም እስከነችግሩ ጉባኤው ቀጥሏል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤታችንም ጉባኤውን መቀጠል የሁሉም ተሳታፊ የጋራ ሃሳብ መሆኑን እንዲሁም የእቅድ አፈፃፀም የሚገመገምበትና ቀጣይ እቅድ የሚፀድቅበት ከመሆኑ አኳያ እንዳይስተጓጎል በማሰብ ጉባኤው ሲቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በሚል ተሳትፎውን ቀጥሏል፡፡
ሆኖም የጠቅላላ ጉባኤው የመጨረሻ አጀንዳ የሆነው የሥራ አመራር ቦርድ አመራሮች ምርጫ በጉባኤያተኛው በኩል መግባባት ያልተፈጠረበት፣ የጋራ ስምምነት ያልተደረሰበት ብሎም ተሳታፊዎች ባለመስማማት ጉባኤውን ጥለው የወጡበት ሁነታ ተፈጥሯል።
ባለስልጣን መ/ቤታችን የትልማ ጠቅላላ ጉባኤ በአጀንዳዎች ዙሪያ ተገቢው ውይይት የሚደረግበት፣ የጋራ ግንዛቤና መግባባት የሚፈጠርበት፣ የማህበሩ አንድነት የሚጠናከርበት እንዲሁም ማህበሩ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ስራዎች አቅም የሚፈጠርበት መሆን እንዳለበት ፅኑ እምነት አለው፡፡
ከዚህ አንፃርም በእለቱ የተፈጠረው ሁኔታ ከጉባኤው የሚጠበቁ ውጤቶች እንዳይሳኩ በማድረግ ማህበሩ የተከፋፈለ እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚገባው ልክ ማረጋገጥ የማይችል እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን በመገንዘብ የስራ አመራር ቦርድ ምርጫ መስተካከልና መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች እንዲስተካከሉ በማድረግ ባለስልጣን መ/ቤቱ አስተባብሮ ሌላ ጊዜ እንዲካሄድ አቅጣጫ በመስጠት ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚከናዎኑ ተግባራት በባለስልጣኑ እውቅና የሌላቸው መሆኑን አሳውቋል። በመሰረቱ የበጎ አድራጎት ተቋማት ዓላማቸው ለህዝብ በጎ ስራ ለማከናዎን ከመሆኑ አኳያ ስራዎች ተገምግመውና ቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠው የሚካሄድና በተባበረ ድምፅ ምርጫ የሚካሄድ መሆን የሚገባው ነው፤
ሆኖም የትልማ ጉባኤ የቦርድ ምርጫ ባልተለመደ መልኩ አባላት የተከፋፈሉበትና ለማህበሩ አደጋ የሚፈጥር ሁኖ መከናዎኑ ግርታን የሚፈጥር ጉዳይ ነው።
የትልማ 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 እንዲሁም ሌሎች መመሪያዎችና የተቋሙ አሰራሮች ጋር በተፃረረ መልኩ ማህበር ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ይኖርበታል የሚለውን መርህ በተቃረነ መልኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጥሪ ተደርጓላቸው በድምፅ ሰጪ ጉባኤይተኛነት የተሳተፉበት መሆኑ፤ 12ኛ ፤ ከቦርድ ምርጫ ጋር በተያያዘ የተካሄደው ክንውን ማህበሩን የሚከፋፍልና አንድነቱ ላይ አደጋ የሚፈጥር መሆኑ እና ማህበሩ የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል የበጎ አድራጎት ሥራ ማከናዎን እንዳይቻል የሚያደርግ መሆኑ፤ እና ጉባኤው ከማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ውጭ የተካሄደ በመሆኑ ምክንያት በትግራይ ልማት ማህበር……ጉባኤ የስራ አመራር ቦርድ ምርጫ በህግ ፊት እውቅና የሌለው ህገ-ወጥ ክንውን ሲሆን በባለስልጣኑ በኩልም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
ከዚህ የቦርድ ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚከናዎኑ ተግባራት፣ ፋይናንስ እንቅስቃሴዎችና ሌሎች ውሳኔዎች በህግ የሚያስጠይቁ መሆኑንም እናስገነዝባለን፡፡
በቀጣይ ባለሥልጣኑ በቅርበት ድጋፍ በሚያደርግበት ሁኔታ ጉባኤ ተካሂዶ የቦርድ አባላት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ አሁን ያሉ/ነባር የቦርድ አመራሮች በባለሥልጣኑ በኩል እውቅና ያላቸው ስለሆነ ማህበሩን የመምራትና የማስተዳደር ሥራን እንዲያከናዉኑ እናሳስባለን፡፡


ምላሽ ይስጡ