የ2017ዓ.ም ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እየተከናወነ ይገኛል።
በውድድሩ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሲሳይ ዮሐንስ እንደገለፁት ይህ ውድድር በሁለቱም ፆታ አዋቂዎችና ታዳጊዎችን በማወዳደር በቀጣይ ግንቦት ወር 2017 ዓ.ም በማዳጋስካር በሚደረገው የምስራቅ አፍሪካ የአዋቂዎች ሻምፒዮና ውድድር ላይ የሚሳተፉትን ተወዳዳሪዎች ለመለየት እንዲሁም በመጪው ሐምሌ ወር በናይጀሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ የታዳጊዎች ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፍ ብሔራዊ ቡድን አባላትን ለመምረጥ ያሰበ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጠረጴዛ ቴኒስ ያላት ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ እያሳየች ትገኛለች ፤ ኢትዮጵያ ከ45 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በምንይዘው ግንቦት ወር በኳታር ዶሃ በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ አራት ሴትና አንድ ወንድ ለብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ መቻሏ አንዱ አመላካች ነጥብ ነው።
የኢትዮጵያ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸው ይህ የበጀት ዓመቱ ሁለተኛው ዙር መርሃ ግብር መሆኑን ጠቅሰው ክለቦች የስልጠናቸውን ውጤት እና የልጆቹን አቅም ለመፈተሽ የሚረዳ እና በሀገር ደረጃም የአዋቂዎችና የታዳጊ ስፖርተኞችን በዕድሜያቸው ልክ ጥሩ አቅም ያላቸውን ስፖርተኞችን ለመለየት ያስችላል ብለዋል።
በዚህ የክለቦች ውድድር አስር ክለቦች የሚወዳደሩ ሲሆን የትግራይ ክልል ቴኒስ ቡድን በተጋባዥ እንግድነት እየተሳተፈ ይገኛል።
ውድድሩ በሁለቱም ፆታ በነጠላና በቡድን በአዋቂዎችና በታዳጊዎች የዕድሜ ክልል በማወዳደር ከሚያዝያ 27-30/2017ዓ.ም እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመላክታል።
ምላሽ ይስጡ