በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ደንብ እና መመሪያ ተላልፈዋል የተባሉ ወደ 28 የሚጠጉ ሆቴሎች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው፣ የከተማ አስተዳደሩ ባህል ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል፡፡
ቢሮው ከወራት በፊት በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ የከተማዋ አገልግሎት ሰጭዎች ላይ፣ አስተናጋጆቻቸው ከአለባበስ ጀምሮ እስከ ፀጉር አቆራረጥ የሚዳስስ 2 ዓመት በጥናት የቆየ ደንብ አዘጋጅቶ ማፅደቁ ይታወቃል፡፡
ከጸደቀ ወራትን ያስቆጠረው ይህ ደንብ አተገባበሩ እና ተፈጻሚነቱ ምን ይመስላል ሲል መናኸሪያ ሬዲዮ ቢሮውን ጠይቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪስት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ገነት ይመር ለጣቢያችን በሰጡት ምላሽ፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በተለይም በሆቴሎች እና በሬስቶራንቶች፣ ስለጸደቀው ደንብ ባለው የግንዛቤ እጥረት፣ በፍጥነት ወደ እርምጃ አለመግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በተለያዩ መንገዶች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መቆየቱን ገልጸው፣ ከመጋቢት ወር ጀምሮ፣ የመጀመሪያ ደረጃ የማስጠንቀቂያ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡ በዚህም ከመጋቢት ወር ጀምሮ፣ 28 የሚደርሱ ሆቴሎች እና፣ ሬስቶራንቶች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አመላክተዋል፡፡
በደንቡ መሰረት ተግባራዊ የማያደርጉ ሆቴሎች ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ 50 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ሲሆን፣ በቅጣቱ የማይመለሱትን ደግሞ የስራ ፈቃዳቸው እንደሚነጠቁ መመላከቱም ይታወሳል፡፡
ምላሽ ይስጡ