በእግሊዝ ኖርዘምበር ላንድ የሚኖረው የ26 ዓመቱ ወጣት ጄምስ ብራውን ለእሳት አደጋ ሰራተኞች ካለው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ በዚህ ስራ ለመሳተፍ ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ይሁንና ከአለባበሳቸው እስከ ስራቸው የሚማርኩትን ሰዎች በስራ ላይ እያሉ የማየት አምሮቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይሔዳል፡፡
እንደመፍትሔ የወሰደውም ወደ እሳት አደጋ መከላከያ ቢሮው በተለያዩ ጊዜያት በመደወል ድምጻቸውን መስማትና አደጋ ደርሶ በስራ ላይ ሲሰማሩ በርቀት ማየት ሆነ፡፡ በስተመጨረሻም ወጣቱ ጄምስ ብራውን ስራቸውን ቀረብ ብሎ ለማየት ያስችለኛል በሚል በውድቅት ሌሊት የገዛ ቤቱን በእሳት አያይዞታል፡፡
የድረሱልን ጥሪ የደረሳቸው የእሳት ማጥፊያ ብርጌድ አባላት ደርሰው በምግብ ማብሰያ ክፍል ያስነሳውን እሳት ከጅምሩ ብዙም ሳይስፋፋ ለጥንቃቄ ሲባል ምንም አይነት ሶኬት እንዳይሰካ ነግረውት ይሔዳሉ፡፡
እሳቱ በሚነድበት ሰዓት የሚፈጥረውን ቀለም እየተመለከት ሲደስት የነበረው ወጣት ግን ታግሶ መቆየት የቻለው ለ90 ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ እንደገና ሌላ እሳት እንዲነሳ በማድረግ መደወሉ ያጠራጠረው ፖሊስ ምርመራ ሲያደርግ ሆን ብሎ እሳቱን እንዳስነሳው ደርሶበታል፡፡
ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤትም ዳግም ተመሳሳይ ድርጊት ቢፈጽም በእስር እንደሚቀጣው በመግለጽ ለጊዜው ለቆታል ያለው የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ነው፡፡
ምላሽ ይስጡ