በተያዘው አመት መስከረም ወር ላይ የተጀመረው የስነ-ህዝብና ጤና ቆጠራ ባለፉት 8 ወራት ውስጥ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች በተሰራው ስራ ከግማሽ በላይ የሚጠበቀውን ስራ ማጠናቀቅ እንደተቻለ ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሳፊ ገመዳ ናቸው፡፡
በሃገራችን ይህ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚገልጹ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ሳፊ፣ በሃገራችን የዜጎችን አመታዊ ፍጆታና ገቢ ምን እንደሚመስል ለማወቅ የሚለው ዋናው አላማው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ከድህነት ወለል በታች ሆነው የሚኖሩ ዜጎችን በአግባቡ የመለየት ስራውን ለመስራትና ለመንግስት ለማሳወቅ ይህ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት ሚናው የጎላ እንደሆነ አቶ ሳፊ ተናግረዋል፡፡
የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናቱን፤ በስታስቲክስ አገልግሎትና በሌሎች 5 ተቋማት በኩል የምልመላ ስራውን በማከናወን 620 የሚሆኑ ወጣቶች በየክልሉ ዘመናዊ ታብሌቶችን ይዘው እንዲሰሩ መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ጥናቱ የእናቶችን፣ የህፃናትንና የወጣቶችን የጤና ሁኔታ ያማከለ ስራ ለመስራት ሲባል የአመጋገብ ሁኔታቸውን የመከታተልና እንዲሁም የክብደት መጠናቸውን መለኪያ ዘመናዊ ሚዛን ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ አቶ ሳፊ ገልጸው፣ ስራው በነሃሴ መጨረሻ 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡
በሃገራችን እንደዚህ አይነት የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናቶች መካሄዳቸው የዜጎችን የኑሮ ፣ የአመጋገብ ሁኔታና እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ለይቶ ለማወቅ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ