👉ተጠባቂ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታን ይዞ በዛሬው እለት ኤምሬትስ ስቴዲየም ላይ ይመለሳል
አርሰናልን ከ ፓሪስ ሴንት ጄርሜ ጋር የሚያገናኘው ይህ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የበርካታ እግርኳስ ቤተሰቦች የሚጠብቁት አጓጊ መርሀ-ግብር ነው።
መድፈኞቹ ፤ አርሰናሎች ዛሬ በሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ሆነው ብቅ ሲሉ ከ19 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደርገዋል። የ6 ቀን እረፍት የሚያገኘው ቡድን አርሰናል የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውንም ሜዳቸው ላይ እንደማከናወናቸው መጠን ጨዋታውን ለማሸነፍ ቅድሚያ ግምት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ ተገናኝተው አርሰናል ጨዋታውን 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ መቻላቸው አይዘነጋም ፤ ያኔ የነበረው የፒ ኤስ ጂ ቡድን ግን አሁን ካለው ጋር በቅንጅት እና ውህደትም ፤ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና በስብስብ ደረጃም ልዩነቶች አሉት።
ያኔ ኦስማን ዴምቤሌ በባህሪ ችግር ምክንያት በስብስቡ ውስጥ ያልተካተተ ሲሆን ክቪካ ክቫርሽክሊያ ደግሞ ስብስቡን ገና ያልተቀላቀለ ተጫዋች እንደነበር የሚታወስ ነው።
ሁለቱ ክለቦች የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ሁለቱም ይሄንን ባለ ግዙፍ ጆሮ ዋንጫ ክብር አሳክተው አለማወቃቸው እንዲሁም ሁለቱም ቡድኖች በስፔናዊ ታክቲሺያኖች መመራታቸው ያመሳስላቸዋል። በዛሬው የኤምሬትስ ፍጥጫ ጥቃቅን ጉዳዮችም በዚህ ጨዋታ ላይ ትልቅ ቁምነገር ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል።
ፒኤስ ጂዎች ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳቸው ፓርክ ደ ፕሪንስ በኒስ 3-1 በመሸነፍ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሽንፈት ካጋጠማቸው በኋላ ነው ከአርሰናል ጋር በሻምፒዮንስ ሊጉ የሚገናኙት። የቡድኑ ስነ ልቦና ጥያቄ የሚፈተንበት ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ከቡድን ዜናዎቻቸው ጋር በተያያዘ የእንግዳው ቡድን አሰልጣኝ ልዊስ ኤንሪኬ ጠንካራ ስብስባቸው ለንደን ይዘው ብቅ ይላሉ ተብሎ ይገመታል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ በሜዳቸው የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሽንፈት ሲያጋጥማቸው ዴምቤሌን ጨምሮ የቡድኑ አምበል ማርኪንሆስ ፤ ባርኮላ እና ኬቫርሽኬሊያ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ቢካተቱም ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን ተቀይረው ወጥተው እንዲያርፉ ተደርጓል።
ከዋ ውጪ የቡድኑ ሌላው ቁልፍ ተጫዋች አችራፍ ሀኪሚ በዚህ የሻምፒዮንሊግ ምዕራፍ 1 ጎል አስቆጥሮ 5 ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። የአሰልጣኝ ኤንሪኬ ሌላው ቁልፉ መሳሪያ ሲሆን ከማርቲኔሊ ጋር የሚያደርጉት ሰላማዊ ፍልሚያ ይጠበቃል በተረፈ ሁሉም ተጓዥ የፒሬስ ጂ ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
በሚኬል አርቴታው ቡድን ሚኬል ሜሪኖ ከቡድኑ ጋር የተሳካ ሙሉ ልምምድ በትላንትናው እለት ማከናወኑ መልካም ዜና ያደርገዋል። ከዛ ውጭ ቤን ዋይት እና ካሊያፊዮሪም በዛሬው ጨዋታ የስብስቡ አካል የመሆናቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ተብሏል።
ጊብራዬል ማጋሌሽን ጨምሮ ጋብሬል ሄሱስ ፤ ካይ ሀቨርትዝ ፤ ታኬሂሮ ቶሚያሱ ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ የሚያርቃቸው ጉዳት ስላጋጠማቸው ከዚ ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ሚኬል አርቴታ በዚህ እግርኳስ ክለብ ውስጥ ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚደረግ ትልቅ ጨዋታ ነው ፤ ደጋፊዎቻችን ያላቸውን ማልያ ፤ ስካርፍ ፤ ሁሉ ይዘው ታይቶ የማይታወቅ ድባብ ይፈጥሩልናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል ሀሳብ የሰጠ ሲሆን ልዊስ ኤንሪኬ በበኩሉ አርሰናል በሚኬል አርቴታ ስር አውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ ምርጥ ክለቦች መካከል አንዱ መሆን ችሏል ግን ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ በአርሰናል ከተሸነፈው ቡድን በጣም የተሻለ ቡድን አሁን እንዳላቸው ጎን ለጎን አስገንዝቧል።
የፒኤስ ጂ ተጓዥ ደጋፊዎች ቁጥር ከ3000 ወደ 2500 ዝቅ እንዲል መደረጉ ያስከፋቸው የፒኤስ ጂ ክለብ አመራሮች ቅሬታቸውን ለUEFA አስገብተዋል። ይህ የሆነው በለንደን ያለው የፀጥታ ሀይሎች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሆኑም ተገልጿል።
አርሰናል ጨዋታውን ለማሸነፍ ምን የተለየ አቀራረብ ይዞ ብቅ ይላል ፤ የቶማስ ፓርቴ በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አለመኖርን ተከትሎ የፒ ኤስ ጂ 5-2-3 የሚመስል በጣም Fluidity ያለው ሜዳ ላይ ከሚገኘው ሁሉም ተጫዋች ኳስ ለመቀበል ወደ ኳሱ የሚሄዱ የአማካኝ መስመር ተጫዋቾችን ለመቋቋም ምን የተለየ ቀመር ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል የሚሉት ጉዳዮች ሁሉ ይጠበቃሉ።
አርሰናል ከ2006 በኋላ ለፍፃሜው ለመብቃት እንዲሁም የፈረንሳዩ ሀያል ክለብ ከ2020 በኋላ የፍፃማውን የሙኒክ ቲኬት ለመቁረጥ ተፋጠዋል።
ጨዋታው ምሽት 4:00 ሲል ሰሜን ለንደን ኤምሬትስ ስቴዲየም ላይ ይጀምራል ፤ ስሎቬንያዊው ምስጉን ዳኛ ስላቭኮ ቪንሲች ጨዋታውን በመሀል አልቢትርነት የሚመራው ይሆናል።
ምላሽ ይስጡ