በአዲስ አበባ ከተማ አዳዲስ በሚገነቡ ትምህርት ቤቶች፣ በሁሉም ዘርፍ የልዩ ፍላጎት ወይም ስፔሻል ኒድ ተማሪዎችን ታሳቢ ተደርገው እንደሚገነቡ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል፡፡
በነባር ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ያማካለ የትምህርት አሰጣጥ እንዲኖር፣ ጥረት ሲደረግ እንደቆየም ቢሮው አንስቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ ለመናኸሪያ እንደተናገሩት፣ በተለይም ከዚህ ቀደም የስፔሻል ኒድ ወይም የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች፣ በሳይንስ እና ፈጠራ እንዲሁም የኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ የነበራቸው ተሳትፎ እምብዛም እንደሆነ በማስታወስ፣ አሁን ላይ ቢሮው ልዩ ድጋፋ የሚሹ ተማሪዎች፣ በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ በሳይንስ እና ፈጠራ እንዲሁም የኪነ ጥበብ ስራዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም ቢሮው ለእነዚህ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች አስቻይ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው አሰራሮችን ክፍት በማደረግ ልዩ ትኩረት እየሰጠ መሆኑንም አቶ ዲናኦል ተናግረዋል፡፡
ቀጣይ በከተማዋ የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች በሁሉም ዘርፎች ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎችን ታሳቢ ተደርገው እንደሚገነቡም አመላክተዋል፡፡
ከቀናት በፊት በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ 10ኛው ሳይንስና ፈጠራ ስራ ኤግዚቢሽን አካል ጉዳተኞች እና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የተለያዩ የፈጠራ እና የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ማቅረባቸውንም አንስተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ