የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በተያዘው የበጀት አመት በዘጠኝ ወራት አፈፃፀም በስፋት ከሰራኋቸው ስራዎች አንዱ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን መቆጣጠር ነው ብሏል ።
በዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን መነሻ ያደረገ የንግድ ስርዓት እንዳይኖር ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 9 ሺሕ 134 የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገ ቁጥጥርና ነጋዴዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ42 ቢሊየን በላይ ገንዘብ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ መደረጉ ተገልጿል ።
ቢሮው ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ህገወጥ ነጋዴዎችንና ብልሹ አሰራር ብሎም የጎዳና ላይ ንግዶችን መቆጣጠሩን የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ናቸው።
በተለይም አላግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ብሎም ሃሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በመጠቀም ህብረተሰቡን በማጭበርበር ላይ የተሰማሩ እንዲሁም ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ላይ የቁጥጥርና እርምጃ የመዉሰድ ስራዎች በስፋት መሰራታቸውን አመላክተዋል። የኮሪደር ልማቱ ላይ ያሉ የህግ ጥሰቶችንና ህጋዊ ያልሆኑ ነጋዴዎችንም በመቆጣጠር ወንጀልና ደንብ ጥሰትን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል ።
ቢሮው በኑሮ ማረጋጋትና በህገ-ወጥ ንግድ ዙሪያ ክትትልና ቁጥጥር ላይ ትኩረት ሰጥቷል ያሉት ሃላፊዋ፤ ወደ ፊትም ህግና ስርዓት ከማስከበርና የነዋሪውን ሰላምና ደህንነት ከዚህ በተሻለ ለማስጠበቅ በተሻለ የቴክኖሎጂ አሰራር ለመስራት መታቀዱን አመላክተዋል ።
ምላሽ ይስጡ