የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለግል ኩባንያዎች ነዳጅ እንዲያቀርቡ መፈቀዱን ተከትሎ ባካሄደው ዓለም አቀፍ ጨረታ 4 ኩባንያዎች አሸናፊ መሆናቸውን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እስከ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ተጫራቾችም ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ማስያዣ እንዲያቀርቡ ተጠይቀው ነበር፡፡
የድርጅቱ የአቅርቦት እና የሽያጭ መመሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ አወል አሸናፊዎቹ ኩባንያዎች BB Energy፣ Vitol Bahrain፣ Trafigura እና BGN International DMCC መሆናቸውን ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በቴክኒክና በፋይናንስ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው ጨረታውን አሸንፈዋል ያሉት አቶ አባይነህ ኩባንያዎቹ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የነዳጅ አቅርቦት ውል በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መሠረት በማቅረብ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ይሰራሉ ብለዋል፡፡
በጨረታው ከ15 በላይ ኩባንያዎች ቢሳተፉም፣ የተቀመጡትን መስፈርቶች ሟሟላት የቻሉት 4ቱ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡
አቶ አባይነህ አክለውም፣ የተሰጠው የአቅርቦት ፍቃድ ለአንድ ዓመት ብቻ የሚሰራ ሲሆን፣ በዓመቱ ማብቂያ ላይ አዲስ ጨረታ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
ይህ አዲስ አሰራር የነዳጅ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እና ለግል ተሳታፊዎች እድል በመፍጠር የነዳጅ ገበያውን ሊያነቃቃ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ምላሽ ይስጡ