በአለም አትሌቲክስ ኤሊቴ ፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የለንደን ማራቶን እንደሆነ ይታወቃል። ዘንድሮ ከ55 ሺሕ በላይ ሯጮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይገመታል።
ከነዛ መካከል አንዱ የበርካታ ክብሮች ባለቤቱ እንዲሁም በማራቶን ርቀት 3ኛው ፈጣን ሰአት ባለቤት የሆነው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ይጠቀሳል። አምና የለንደን ማራቶንን 2ኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቁ አይዘነጋም። በዘንድሮው ውድድር ግን አትሌቱ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት የፊታችን እሁድ ከሚደረገው የለንደን ማራቶን ውጪ መሆኑን አሳውቋል።
ቀነኒሳ በ2008ቱ የወፍ ጎጆ እየተባለ በሚጠራው የቤጂንግ ኦሎምፒክ 3 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ወርቃማ ታሪክ ያለው ብቸኛው አትሌት እንደሆነ ይታወቃል።
ቀነኒሳ በዚህ ውድድር ላይ ከ4 ጊዜ የለንደን ማራቶን አሸናፊ ከሆነው ኬንያዊው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ ጋር የሚያደርጉትም ትንቅንቅ ተጠብቆ ነበር ፤ የታሰበው ሳይሆን ቀርቷል። ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ታምራት ቶላ ባሳለፍነው ክረምት በተደረገው የፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ ያስገኘ አትሌት እንደነበር የሚታወስ ነው። ኬንያዊው አትሌት ኪፕቾጌን ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አምበሳው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባጋጠመው ድንገተኛ ጉዳት ማዘኑን በመግለጽ በውድድሩ ለሚሳተፉ ሌሎች አትሌቶች መልካም እድል እንዲገጥማቸው መልካም ምኞቱን ገልጿል።
የማራቶን ውድድር ሲነሳ በዚህ ርቀት ፈርጦቹን ሁሌ የሚያገናኘው የለንደን ማራቶን በልዩነት ደግሞ ሁለት የውድድሩ አውራ ሊባሉ የሚችሉ ሴት አትሌቶችን ሲፈን ሀሰን እና ሩት ጄፒንጌችን የሚያፎካክር ውድድር ስለሆነ ከወዲሁ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ከመሆኑም በተጨማሪ የቦታው ሪከርድ መሻሻሉ እንደማይቀር ብዙዎች ከወዲሁ እየገመቱት የሚገኘው ሀሳብ ነው።
በ1981 እንደተጀመረ የሚነገረው ተጠባቂው የለንደን ማራቶን የፊታችን እሁድ ለ45ኛ ጊዜ በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ ላይ የሚከናወን ይሆናል።
ምላሽ ይስጡ