ፍርድ ቤቱ ብርቱካን ተመስገንን ጨምሮ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የ14 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል፡፡
ፖሊስ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት እስካሁን በተጠርጣሪዎች ላይ ያሰባሰባቸውን መረጃዎች እና ቀሪ የምርመራ ሥራዎችን አጠናቅቆ አቅርቧል፡፡
ብርቱካን ተመስገንን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙኃን ከተላለፈው ሐሰተኛ ዘጋቢ ፊልም ጋር በተያያዘ ብርቱካን ተመስገን፣ ነብዩ ጥዑመልሳን የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ፣ ታሪኩ ኃይሌ የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ፣ ደረጀ ሉቃሌ፣ ኅሊና ታረቀኝ፣ ንጥር ደረጀ እና መታገስ ዓለሜ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይም ስልጣንን በኃይል ለመያዝ፣ የጦር መሣሪያ በመታጠቅ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ በመደራጀት፣ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ጽንፈኛና ፀረ ሰላም ቡድን አመራሮች ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ መንግሥት የሕዝብ ተቀባይነት እንዲያጣና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ እንዲደረግበት በማሰብ፣ ተዋድደውና ተከባብረው በሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠርና ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ፣ በውጭ ሀገር ከሚገኝ የፀረ ሰላም የቡድን አመራሮች ጋር በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመገናኘት እና ተልዕኮ በመቀበል የሥራ ባህሪያቸውን እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም የሚሉ የምርመራ የጥርጣሬ መነሻዎች ለችሎቱ ቀርበዋል፡፡
የምርመራ ሥራውን በሰውና በሠነድ ማስረጃ በስፋት በማጠናከር የፎረንሲክ እና የቴክኒክ ምርመራዎችን በተሰጠው 12 ቀናት አጠናቅቆ ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን ፖሊስ አስረድቷል።
የተከሳሽ ጠበቃዎች በበኩላቸው÷ ተጠርጣሪዎቹ ቋሚ አድራሻ ያላቸው እና መረጃም የማያጠፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የዋስትና መብታቸው ሊከበር ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣዎቹ የዋስትና መብት ቢፈቀድላቸው መረጃ ሊሰውሩ እንደሚችሉና ምስክሮችንም በጥቅም ሊደልሉብኝ ይችላሉ ሲል ተቃውሟል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዓቃቤ ሕግ የ14 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ መፍቀዱን ፋ.ሚ.ኮ ዘግቧል፡፡
ምላሽ ይስጡ