በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የጅቡቲ መንግስት በሀገሪቱ የሚኖሩና ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማስታወቁን ተከትሎ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊዎች ጋር የተደረገው ውይይት አለመሳካቱን ኤምባሲው በማህራዊ ትስስር ገጹ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
በቀጣይም ጅቡቲ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎች በቁጥጥር ስር በማዋል ልታስወጣ እንደምትችል ተመላክቷል፡፡ ውሳኔውም በርካታ የኢትዮጵያ ዜጎች በጅቡቲ እንደመኖራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ተፅዕኖ ሊያሳድርባቸው እንደሚችል ይታመናል፡፡
ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያና ጅቡቲ ጠንካራ ወዳጅነትና ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የሚያካሄዱ ሀገራት እንደመሆናቸው መጠን ኢትዮጵያ ምን አይነት ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶችን መከተል ይገባታል ያልናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ዘላቂ ወዳጅነትን ማዕከል በአደረገ መልኩ ማስኬድ ይገባል የሚል ሃሳብ አንስተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያና መምህሩ አቶ እያሱ ኃይለሚካኤል የጅቡቲ መንግስት ውሳኔዎች የሁለቱን ሀገራት ድፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ሊያሻክር የሚችልና በጥንቃቄ መታየት ይገባዋል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ፖልሲ ለዜጎቿ ክብር ትኩረት የሚሰጥ እንደመሆኑ ፈጣን እልባት ሊሰጠው እንደሚገባና ቀጣይ ግንኙነቶችን ከሚያሻክር አካሄድ ይልቅ የሁለቱንም ሀገራት የጋራ ጥቅም ባከበረ መልኩ መስራት እንደሚገባ አቶ እያሱ ተናግረዋል፡፡
በቀጠናዊና ብሄራዊ ጥቅም ዙሪያ በቅርበት እየሰሩ የሚገኙት ረዳት ፕሮፌሰር ታምራት ከበደ በበኩላቸው መሰል ውሳኔዎች የሁለቱን ሀገራት ጥቅም ባስከበረ መልኩና ዘላቂ ወዳጅነትን ከግምት በማስገባት መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
የጅቡቲ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያ ሰነድ ሳይኖራቸው በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ከመጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ፤ ይህንን የማይተገብሩ ደግሞ በፖሊስ ሀይል ወደመጡበት ሀገር እንዲመለሱ እንደሚያደረግ ማሳወቁን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማህራዊ ትስስር ገጹ በአጋራው መልዕክት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
__
ምላሽ ይስጡ