በትግራይ ክልል ከ75,000 በላይ የሚገመቱ የቀድሞ ታጋዮችን ትጥቅ የማስፈታትና በዘላቂነት ወደ መደበኛ ሕይወት ለማስገባት የታቀደው የተሃድሶ ሥልጠና በክልሉ በተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት ምክንያት ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በክልሉ አሁን ላይ የፖለቲካ ውጥረቱ በመርገቡ እና የፌዴራል መንግስቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ስልጠናው ዳግም ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም መጀመሩን ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ከ7,000 በላይ የቀድሞ ታጋዮች በመቀሌ እና ህዳጋ ሃሙስ የሥልጠና ማዕከላት ሥልጠናውን እንደወሰዱ የገለጹት ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ መሰለ ምንም እንኳን በተያዘው የበጀት ዓመት ከ75,000 በላይ የሚሆኑ የቀድሞ ታጋዮችን በሥልጠናው ለማካተት ዕቅድ ቢይዝም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ግብ በተያዘው ጊዜ ውስጥ ማሳካት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
የተሃድሶ ሥልጠናው ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን ወደ 15,000 የሚጠጉ የቀድሞ ታጋዮች ብቻ ሥልጠናውን የወሰዱ ሲሆን ይህም የታቀደውን ግብ ለማሳካት በዚህ አመት አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው የገለጹት።
በተጨማሪም በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ371 ሺህ በላይ ፍላጎት ያላቸው የቀድሞ ታጋዮች የተሃድሶ ሥልጠና እንደሚያስፈልጋቸው የገለጸው ኮሚሽኑ፣ እስካሁን በአራት ክልሎች ብቻ 25,000 የሚሆኑት ሥልጠናውን መውሰዳቸውን አቶ ሃብታሙ ተናግረዋል።
በትግራይ ፣በአማራ፣ኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች የተመዘገቡትን የቀድሞ ታጣቂዎች ለማሳተፍ ከፍተኛ የሆነ በጀት እንሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
የተሃድሶ ሥልጠናው ብቻውን በቂ እንዳልሆነና ከሥልጠናው በኋላ የቀድሞ ታጋዮች በዘላቂነት ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ የሚያስችላቸው የሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ሃብታሙ ፣ በተጨማሪም በዚህ ረገድ የሚታዩ የበጀት ክፍተቶችን ለመሙላት የክልል መንግሥታትና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምላሽ ይስጡ