በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ20 ሺሕ የሚበልጡ ሴቶች ወደ ወሲብ ንግድ መግባታቸውን የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል።
በክልሉ ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የኢኮኖሚ ችግር በወሲብ የሚተዳደሩ እና ወደ ጎዳና የወጡ ሰዎች ቁጥራቸው መጨመሩን የቢሮው የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያ እና መከታተያ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ጸጋ ተናግረዋል።
ባለፉ ዘጠኝ ወራት ከ20 ሺሕ የሚበልጡ ሴቶች ወደ ወሲብ ንግድ መግባታቸውንና ከ9 ሺሕ በላይ ህጻናት ጎዳና ተዳዳሪ መሆናቸውን፤ከ7 ሺሕ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ወደ ልመና መግባታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ቢሮው የጸጥታዉ ችግር ባልከፋባቸዉ ስፍራዎች ብቻ ይህንን ማረጋገጡን የገለጹት ዳይሬክተሩ በጸጥታው ችግር ምክንያት ግን በርካታ ወረዳዎች ላይ ጥናት አለመደረጉን አንስተዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም በጸጥታው ችግር ምክንያት ማህበራዊ ችግር ውስጥ የገቡ ሰዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት የኢኮኖሚ ችግርም አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። የኢኮኖሚው ችግር እንዲመጣ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የጸጥታው ጉዳይ ዋነኛው መሆኑን አመላክተዋል።
ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ክልሉ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ሴቶች እንዲሁም ወደ ጎዳና የወጡ ሰዎችን የስራ እድል የሚያገኙበት ሁኔታን ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ሃምሌ ወር 2017 ዓ.ም ከዚህ ቀደም ባልተካተቱ ወረዳዎች ጥናቱን በማድረግ መረጃን የማጥራት ስራ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ