ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ዛሬ በትልቁ እና ግዙፉ ቦስተን ማራቶን ላይ ለኬንያውያን አትሌቶች ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።
በአለም አትሌቲክስ አወዳዳሪው አካል የኤሊት ፕላቲኒየም ደረጃ የሚሰጠው ይህ የቦስተን ማራቶን በዛሬው እለት በቦስተን ሜስተጁሰስ የሚከናወን ይሆናል።
እ.ኤ.አ በ1897 እንደተጀመረ የሚነገርለት ይህ አንጋፋ ውድድር ዘንድሮ ለ129ኛ ጊዜ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል። የቦስተን ማራቶን አለማችን ላይ ረጅም እድሜን ካስቆጠሩ የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ ብቻም ሳይሆን ቀዳሚም ጭምር ነው። ስለዚህ ይህንን ታሪካዊ የማራቶን ውድድር ማሸነፍ እና አንጋፋውን የማራቶን ውድድር በቀዳሚነት ማጠናቀቅ የየትኛውም አትሌት ህልም ነው።
ታዲያ ይሄንን የማራቶን ውድድሮች አውራ እየተባለ የሚጠራው እና አንጋፋው የማራቶን ውድድር አምና በሁለቱም ፆታዎች በቀዳሚነት ውድድራቸውን ያጠናቀቁት በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት ሲሳይ ለማ እና በሴቶች ሄለን ኦቢሪ ክብራቸውን ለማስጠበቅ የሚወዳደሩ ይሆናል።
ኬንያዊቷ ሄለን ኦቢሪ በአትሌቲክስ ታሪክ ማህደር ውስጥ የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ፣ የማራቶን ውድድር እንዲሁም የሀገር አቋራጭ ወይም Cross country በማሸነፍ ቀዳሚዋ አትሌት ናት።
የፈረንጆቹ አዲስ አመት በገባበት ያሳለፍነው ጥር ወር ላይ የሂውስተን ግማሽ ማራቶንን ላይ ተሳትፋ 2ኛ ደረጃን ይዛ ካጠናቀቀች በኋላ በትልቅ መድረክ ላይ ሄለን ኦቢሪን አልተመለከትናትም ነበር። የ2 ጊዜ የ5000 ሜትር የአለም ሻምፒዮና ሄለን ኦቢሪ አምና እና ካቻምና በቀዳሚነት ያጠናቀቀችውን የቦስተን ማራቶን ዘንድሮም ለተከታታይ 3ኛ ጊዜ አሸንፋ ክብሯን ለማስጠበቅ የምትፎካከር ይሆናል። ይህንን ታላቁ የቦስተን ማራቶን ለተከታታይ 3 ጊዜ በማሸነፍ ታሪክ የሰራችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋቱማ ሮባ ስትሆን ጊዜውም በ1999 ነበር። ይህንን ታሪክ ሄለን ኦቢሪ ለመጋራት ትልቅ ትንቅንቅ እንደምታደርግ ይገመታል።
ይህንን ሀሳቧን እንዳታሳካ ወደ 6 የሚጠጉ እንዲሁም ሰአታቸው 2 ሰአት ከ20 ደቂቃ ባነሰ ሰአት የገቡ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ቦስተን ላይ ይገኛሉ። ከነሱ መካከል የ2 ጊዜ የቦስተን ማራቶን አሸናፊዋ ኤድና ኪፕላጋት እንዲሁም የ2022 የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊዋ ሻሮን ሎኬዲ ይገኙበታል።
በወንዶቹ ኢትዮጵያዊው ሲሳይ ለማ የዘንድሮውንም ክብር ለማሳካት ቅድሚያ ግምቱን ዪገኘው አትሌት ነው። ይህ አትሌት የአምና የቦስተን ማራቶን አሸናፊ አትሌት ነው። ከዛ ውጪ አምና ታህሳስ ወር ላይ የቫሌንሺያ ማራቶንን 2:01:48 በመግባት በቀዳሚነት ውድድሩን ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። የገባበት ሰአትም የአለማችን 4ኛው ፈጣን ሰአት ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል።
ከዛም በፊት በ2021 የለንደን ማራቶንን በቀዳሚነት ነበር ውድድሩን ያጠናቀቀው። ቦስተን ላይ ግን አምና ውድድሩን በበላይነት እስኪያጠናቅ ድረስ አትሌት ሲሳይ ጥሩ ሪከርድ አልነበረውም ፤ በ2017 ውድድሩን ማጠናቀቅ አልቻለም ነበር ፤ በ2019 ደግሞ 30ኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው።
አምና ውድድሩን 2:06:17 በመግባት ነበር በቀዳሚነት ያጠናቀቀው ከዛ በፈጠነ ሰአት ለማጠናቀቅ እንደሚሞክር ቢናገርም ጠንካራ ሌሎች ተፎካካሪ አትሌቶች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም። የዚ ውድድር ሁለት ጊዜ አሸናፊ እና አምና 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኤቫንስ ቼቤትን ጨምሮ የቺካጎ ማራቶን አሸናፊው ጆን ኮሪር አምና ቦስተን ማራቶንን 4ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው ፤ እንዲሁም የ 2 ጊዜ የቦስተን ማራቶን አሸናፊ ከሆነው ኢትዮጵያዊው አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይገመታል።
በሁለቱም ፆታዎች ውድድራቸውን በቀዳሚነት የሚያጠናቅቁ ተወዳዳሪዎች እናንዳንዳቸው 150,000 ዶላር የገንዘብ ሽልማት ይጠብቃቸዋል። እስከ 10ኛ ደረጃ ይዘው ለሚያጠናቅቁ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማቱ እየቀነሰም ቢሆን በየደረጃቸው ጥሩ እና ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል።
ስለዚህ በኮኮቦች የተሞላ እና ጥሩ ፉክክርም እንመለከትበታለን ተብሎ የሚገመተው የቦስተን ማራቶን በዛሬው እለት ለ129ኛ ጊዜ በአሜሪካ ቦስተን ግዛት በድምቀት የሚከናወን ይሆናል።

ምላሽ ይስጡ