የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ9 መቶ 90 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ፤ የክልሉ መንግስት የይቅርታ አዋጁን መስፈርት ላሟሉ 9 መቶ 90 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር ያሳዩና በሕግ በተደነገገው አግባብ የይቅርታ መስፈርትን ማሟላታቸው በክልሉ መንግስት የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የሕግ ታራሚዎቹ በመደበኛ የይቅርታ ሕግ እና ሌሎች ተጨማሪ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ተብለዉ በልዩ ሁኔታ የቀረቡ፤ በማረሚያ ቆይታቸው ስለመታረማቸውና ስለመታነፃቸው ማረጋገጫ የቀረበላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የይቅርታው ተጠቃሚዎች በይቅርታ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እና አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ይቅርታ በማያስከለክሉ ወንጀሎች ተሳትፈው፡-
በማረሚያ ቤት የቆዩ፤ በጤና ችግር፤ በዕድሜ መግፋትና ከሕጻናት ጋር አብረዉ የታሰሩ እንዲሁም ከተፈረደባቸው ሲሶ (1/3) እና ከግማሽ (1/2) በላይ የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
አክለው ይቅርታው ከተደረገላቸው 9 መቶ 90 የሕግ ታራሚዎች መካከል፡- 9 መቶ 85ቱ በሙሉ ይቅርታ ከእስር የሚፈቱ ሲሆን፤ ቀሪ 5 ታራሚዎች የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የይቅርታ ተጠቃሚ ከሆኑት የሕግ ታራሚዎች መካከል 73ቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ 9 መቶ 17ቱ ደግሞ ወንዶች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የሕግ ታራሚዎች የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥና አምራች ዜጋ በመሆን የበደሉትን ህብረተሰብ በማገልግል በልማት ሊክሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ህብረተሰቡም ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች በፈፀሙት ጥፋት የተፀፀቱና በአግባቡ ታርመው የወጡ መሆኑን በመረዳት መልካምና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግላቸው ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ምላሽ ይስጡ